ቢዝነስ

ቤአኤካ ጠቅላላ የንግድ ሥራና ሻክማን የተባለ የውጭ ኩባንያ በኢትዮጵያ ከባድ ተሽከርካሪዎችን መገጣጠም ሊጀምሩ ነው

By Meseret Awoke

February 23, 2023

አዲስ አበባ፣ የካቲት 16፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ቤአኤካ ጠቅላላ ንግድ ሥራ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር እና ሻክማን ከተባለ ዓለም ዓቀፍ የአውቶሞቲቭ አምራች ኩባንያ በኢትዮጵያ ከባድ ማሽነሪዎችና ተሽከርካሪዎችን መገጣጠም ሊጀምሩ ነው።

የሁለቱ ኩባንያዎች በጋራ ስራ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር በአዲስ አበባ ወዳጅነት ፓርክ ተካሂዷል።

በመርሐ ግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት የቤአኤካ ጠቅላላ የንግድ ሥራ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ሚካኤል ካሣ ፥ ከሻክማን ግሩፕ ጋር በመተባበር ማሽነሪዎችና ተሽከርካሪዎችን የመገጣጠም ስራው ይከናወናል ብለዋል።

በሦስት የትግበራ ምዕራፍ የተከፋፈለ የትግበራ ስምምነት መደረጉን ያስታወሱት ዳይሬክተሩ ፥ በመጀመሪያ ዙር በዓመት 1ሺህ 500 ከባድ ተሽከርካሪዎችን በመገጣጠም ለገበያ እናቀርባለን ነው ያሉት።

በሁለተኛው ምዕራፍ ደግሞ በዓመት 3 ሺህ ተሽከርካሪዎችን የመግጠም አቅድ መያዙን ጠቅሰዋል።

ከተሽከርካሪ መገጣጠምና ማምረት በተጨማሪ የዕውቀትና የሙያ ክህሎት ሽግግርና የሰው ኃይል ሥልጠና ይከናወናልም ነው ያሉት።

ከሚገጣጠሙት መካከል ካሶኒ፣ ሎቤድ፣ የፍሳሽ ጭነት ተሽከርካሪ ሃይቤድ ከባድ ተሽከርካሪዎች መሆናቸውን ጠቅሰው ፥ ከ45 ቀናት በኋላ ለገበያ ማቅረብ እንጀምራለን ማለታቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።

በስነ-ሥርዓቱ ላይ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል፣ የሻክማን ግሩፕ የሥራ ኃላፊዎች እና ሌሎችም ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።