የሀገር ውስጥ ዜና

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከተመድ ዋና ጸሐፊ እና ከአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት ጋር ተወያዩ

By ዮሐንስ ደርበው

February 18, 2023

አዲስ አበባ፣ የካቲት 11፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ ጎን ለጎን ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ እና ከአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት አኪንውሚ አድሲና ጋር ተወያዩ፡፡

ባደረግነው የሁለትዮሽ ውይይት በሰላም ስምምነቱ አተገባበር እንዲሁም የመንግሥታቱ ድርጅት ለኢትዮጵያ የሚሰጠውን ድጋፍ የበለጠ ማሳደግ በሚቻልበት ዙሪያ መክረናል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ ገልጸዋል፡፡

አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በበኩላቸው በውይይቱ ወቅት የኢትዮጵያ የሰላም ስምምነት የትግበራ ሂደትን አድንቀዋል።

የመንግሥታቱ ድርጅት ኢትዮጵያ እገዛ በምትፈልግባቸው ጉዳዮች ሁሉ ድጋፍ ለማድረግ ያለውን ፍላጎትም አመላክተዋል፡፡

በውይይታቸውም በኢትዮጵያ እና በመንግሥታቱ ድርጅት መካከል ያለው ግንኙነት ይበልጥ በሚጠናከርበት ሁኔታ መክረዋል፡፡

በተመሳሳይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት አኪንውሚ አድሲና ጋር ተወያይዋል፡፡

የልማት ባንኩ ለግብርና ክፍለ ኢኮኖሚያችን በተለይ ለስንዴ ምርታማነት ጥረታችን እና ለሌሎች ቁልፍ ምርቶቻችን የሚያደርገው ያልተቋረጠ ድጋፍ ወሳኝ መሆኑን ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የገለጹት፡፡