አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 30 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ቻይና የኮሮና ቫይረስን የመጀመሪያ ሁለት የህመም ደረጃዎች ለማከም የተጠቀመችባቸውን የባህል መድሃኒቶች ለኢትዮጵያ በድጋፍ መልክ ልትሰጥ ነው።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርና የጤና ሚኒስቴር ከቻይና የባህል ሃኪሞችና ተመራማሪዎች ጋር ቫይረሱን መቆጣጠር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ተወያይተዋል።
ቻይና የባህላዊ መድሃኒቶችን በመጠቀም ስኬታማ በሆነ መልኩ የኮሮና ቫይረስን መቆጣጠር የቻለችባቸውን መንገዶች ለኢትዮጵያ ለማጋራት ፈቃደኛ መሆኗን ገልፃለች።
በተለይ የቫይረሱን ህመም የመጀመሪያ ሁለት ደረጃዎች ለማከም የተጠቀመችባቸውን ሁለት የመድሃኒት ዓይነቶች ለኢትዮጵያ በድጎማ መልክ ለመስጠት መስማማቷን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታውቋል።
ረጅም እድሜ ያስቆጠረውን የኢትዮጵያ የባህል ህክምና ተቋማዊ በሆነ መልኩ ወደ ስራ እንዲገባ ለማድረግ የሚደረገውን ጥረትም በቴክኖሎጂ፣ በቁሳቁስ እና በሙያ እደግፋለሁ ብላለች።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር ኢንጂ.) የኮሮናን ቫይረስ ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ውስጥ እንደ ሀገር ከተጀመሩ ስራዎች ጎንለጎን የቻይና ድጋፍ ትልቅ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ የባህላዊ መድሃኒቶችም ህጋዊ ማዕቀፍ ኖሯቸው ወደ ስራ እንዲገቡ የተጀመረው ጥረት እንዲሳካም የቻይናን ልምድ ኢትዮጵያ ትፈልጋለች ብለዋል፡፡