አዲስ አበባ፣ መጋቢት 30፣ 2012(ኤፍ.ቢ.ሲ) የሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በ 11 ከተሞች የሚገኙ 22 ሺህ የጎዳና ተዳዳሪዎችን መልሶ ለማቋቋም እንቅስቃሴ መጀመሩን አስታወቀ።
ሚኒስቴሩ በተለያዩ ምክንያቶች ኑሮዋቸውን በጎዳና ላይ ያደረጉ ህፃናቶች ፣ ሴቶች እና አረጋውያን በመደገፍ የተሻለ ህይወት እንዲኖራቸው ለማድረግ ከአለም ባንክ ጋር እየሰራ መሆኑን ገልጿል።
በአሁን ወቅት በመላ ሀገሪቱ ከ80 ሺህ በላይ የጎዳና ተዳዳሪዎች እንደሚገኙ ሚኒስቴሩ ይገልፀዋል።
ሚኒስቴሩ አሁን ላይ በ 11 ከተሞች የሚገኙ 22 ሺህ የጎዳና ተዳዳሪዎችን መልሶ ለማቋቋም ከተለያዩ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ጋር ውል በመግባት ላይ እንደሚገኝ ተነግሯል።
ከዚህ ጋር ተያይዞም በ8 ከተሞ የሚገኙ 6 ሺህ 286 የጎዳና ተዳዳሪዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ከ27 አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ጋር ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ውል ፈፅሟል።
በመሆኑም በመቐለ ፣ አዳማ ፣ ደሴ ፣ ሀዋሳ ፣ጋምቤላ ፣ ሀረሪ ፣ አዲስ አበባ እና ድሬ ዳዋ የሚገኙት እነዚህ ተቋማት በዘላቂነት ከጎዳና ህይወት ለማውጣት የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን እያደረጉ ይገኛል።
በቀጣይም በሌሎች ከተሞች ህፃናትን የያዙ እናቶችን ፣ ወጣቶችን እና አረጋውያንን ከጎዳና በማንሳት በዘላቂነት ለማቋቋም የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ተጠናቀዋል ነው የተባለው።
በፀጋዬ ንጉስ