የሀገር ውስጥ ዜና

የኮሮና ቫይረስ ህሙማንን ለሚረዱ የጤና ባለሙያዎች 645 መኖሪያ ቤቶች ተዘጋጁ

By Tibebu Kebede

April 08, 2020

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 30 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ለኮሮና ቫይረስ ህመምተኞች እርዳታ የሚሰጡ የጤና ባለሙያዎች የሚያርፉባቸው ከ645 በላይ የመኖሪያ ቤቶች መዘጋጀታቸውን የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ገለጹ።

ዶክተር ሊያ ታደሰ እንደተናገሩት ይህን ወረርሽኝ በመቆጣጠርና ምላሽ በመስጠት ሂደት ውስጥ ትኩረት የሚሰጠው የጤና ባሙያዎች ጉዳይ ነው።

ይህም የጤና ባለሙያዎቹ ከየትኛውም የኅብረተሰብ ክፍል በተለየ ለበሽታው ተጋላጭና ህይወታቸውን አደጋ ላይ ጥለው ስለሚሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም መሰረት መንግሥት ከምንጊዜውም በላይ የጤና ባለሙያዎችን ለመደገፍና ለመጠበቅ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ነው ያሉት ሚኒስትሯ፥ ለኮሮና ቫይረስ ህመምተኞች እርዳታ የሚሰጡ የጤና ባለሙያዎች የሚያርፉባቸው ከ645 በላይ የመኖሪያ ቤቶች መዘጋጀታቸውን ጠቁመዋል።

ሌሎች ከ600 በላይ የሚሆኑ ደግሞ በዝግጅት ላይ መሆናቸውንም ሚኒስትሯ የተናገሩት።

በሌላ በኩል የኢንፌክሽን መከላከያ ግብዓቶችን ለጤና ባለሙያዎች በየተቋማቱ የማሟላት ሥራ አሁን ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

የእነዚህ ግብዓቶች ተደራሽነት በዓለም አቀፍ ደረጃ ቢሆን እጥረት ያጋጠመ መሆኑን ገልጸው በሃገር ውስጥ ለማሟላት በድጋፍም በግዢም እየተሰበሰበ መሆኑን ጠቅሰዋል።