Exif_JPEG_420

የሀገር ውስጥ ዜና

ትናንት ምሽት ባጋጠሙ ሁለት የእሳት አደጋዎች በንብረት ላይ ጉዳት ደረሰ

By Melaku Gedif

February 10, 2023

አዲስ አበባ፣ የካቲት 3፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ትናንት ምሽት ባጋጠሙ ሁለት የእሳት አደጋዎች በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን የእሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

ትናንት ምሽት 2:53 ሰዓት ላይ በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 በተለምዶ ዶሮ ማነቂያ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ በተነሳ የእሳት አደጋ 13 የንግድ ሱቆች መቃጠላቸው ተገልጿል፡፡

በሌላ በኩል በቡራዩ ከምሽቱ 2:15 ሰዓት ላይ በደረሰ የእሳት አደጋ የዘይት መጭመቂያ፣ የዶሮና የከብት መኖ ማምረቻ አንድ ሼድ ላይ ከባድ ጉዳት መድረሱ ተመላክቷል፡፡

ሁለቱንም የእሳት አደጋዎች ለመቆጣጠር 14 የእሳት መቆጣጠሪያ ተሽከርካሪ፣ አንድ አምቡላንስ አንድ ውሃ የጫነ ቦቴ ከ96 የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ጋር መሰማራታቸው ተጠቁሟል፡፡

በዚህም የእሳት አደጋው በአካባቢው ተዛምቶ የከፋ ጉዳት ሳያደርስ መቆጣጠር መቻሉን ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

በሁለቱም የእሳት አደጋዎች በሰው ላይ የደረሰ ጉዳት የሌለ ሲሆን÷ የንብረት ውድመት ግምትና የአደጋው መንስኤ እየተጣራ ነው ተብሏል።