Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ብሔራዊ የመረጃና ደኅንነት ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ  በመረጃ ኪነ ሙያ ያሰለጠናቸውን ባለሙያዎች አስመረቀ

አዲስ አበባ፣ ጥር 28፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በብሔራዊ የመረጃና ደኅንነት አገልግሎት ስር የሚገኘው ብሔራዊ የመረጃና ደኅንነት ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በመረጃ ኪነሙያ ዘርፍ ያሰለጠናቸውን ባለሙያዎች ዛሬ አስመረቀ፡፡

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ታዜር ገ/እግዚአብሔር አገልግሎቱ ሀገርን የሚመጥን፣ ብሔራዊ ጥቅምና ደኅንነትን የሚያስክብር የሰው ኃይል በማብቃት ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

የመረጃ ሠራተኞች በሥራው ዓለም የሚያገጥሟቸውን ፈተናዎች ሁሉ ተቋቁመው የሀገር ጥቅምና ደኅንነትን የማስከበር አስተዋጽኦ ለመወጣት መዘጋጀት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ ፕሬዚዳንት ወንደሰን ካሳ በአስገራሚ ፍጥነት መረጃዎች የሚለዋወጡበት ዘመን ላይ በመሆናችን የመረጃ ሁኔታዎችን በመረዳት  የደኅንነት ስጋቶችን የሚያስቀር የሰው ኃይል ማብቃት ይገባል ብለዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ  ለተቋሙ የውስጥ አቅም ከመገንባት አልፎ ለባለድርሻ አካላት እንዲሁም ለአቻ ተቋማት ብቁ ባለሙያዎችን በየጊዜው በማሰልጠን ላይ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ተቋሙ የመረጃ ኪነ ሙያ ሰልጣኞችን ሲያስመርቅ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በቀጣይ በመረጃና ደኅንነት ላይ ያተኮሩ የተለያዩ የስልጠና መርሐግብሮችን ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ ነው ተብሏል፡፡

በቀሰሙት ስልጠና የሀገርና ሕዝብን ደኅንነትና ጥቅም ለመጠበቅ የሚሰጣቸውን ተልዕኮ በብቃት ለመወጣት እንደተዘጋጁ ተመራቂዎች ተናግረዋል፡፡

አገልግሎቱ  ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የላከው መረጃ እንዳመላከተው÷ በመጀመሪያ እና በሁለተኛ ዲግሪ ተማሪዎችን ተቀብሎ በመረጃ ኪነ ሙያ እያስተማረ  ያለ ብቸኛ የሀገሪቱ የትምህርት ተቋም ነው፡፡

Exit mobile version