አዲስ አበባ ፣ ጥር 27 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በባቡር መሰረተ ልማት ላይ በተፈፀመ ስርቆት በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ ብቻ ከ80 ሚሊየን ብር በላይ ጉዳት መድረሱን የኢትዮ ጅቡቲ ባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር አስታወቀ፡፡
የፌደራል መንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር መስመር መሠረተ ልማት ላይ በተደጋጋሚ ዘረፋና ስርቆት ተፈፅሞባቸዋል በተባሉ አካባቢዎችን ጎብኝተዋል፡፡
የማህበሩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር አብዲ ዘነበ÷ በኢትዮ ጅቡቲ ባቡር ትራንስፖርት መሠረተ ልማት ላይ በተለያዩ አጋጣሚዎች ከፍተኛ ዘረፋና ስርቆት እየተፈፀመበት መሆኑን ተናግረዋል።
በመሠረተ ልማቱ ላይ በተደጋጋሚ በተፈፀመው ዘረፋ በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ ብቻ ከ80 ሚሊየን ብር በላይ ጉዳት መድረሱን ገልጸዋል።
በመሆኑም የከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ሃላፊዎች ያደረጉት ጉብኝት በተደጋጋሚ እየደረሰበት ያለውን ጉዳት በጋራ ለመከላከልና አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል መሆኑን አመላክተዋል።
በጉብኝቱ የኢትዮጵያ የፌደራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፋንታ፣ የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክ ሚኒስትር ዴኤታ ደንጌ ቦሩ እና ሌሎችም የሥራ ሃላፊዎች መሳተፋቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡