Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በደብረብርሃን ከተማ መዋዕለ ንዋያቸውን ለሚያፈሱ ባለሃብቶች አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ጥር 25፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በደብረብርሃን ከተማ እና አካባቢዋ መዋዕለ ንዋይ ለሚያፈሱ ባለሃብቶች አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን የከተማ አስተዳደሩ አስታውቋል፡፡

የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት እንደገለጹት÷ በደብረ ብርሃን ከተማ እና አካባቢዋ ያለው የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ በከፍተኛ ሁኔታ እየተነቃቃ መጥቷል፡፡

በርካታ የውጭ እና የሀገር ውስጥ ባለሃብቶችም በተለያዩ ዘርፎች መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ፍላጎት ከማሳየት እና ጥያቄ ከማቅረብ ባለፈ ተግባራዊ እንቅስቃሴ መጀመራቸውን አንስተዋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩም የባለሃብቶችን ጥያቄ መመለስ የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት ማድረጉን ነው ምክትል ከንቲባው የገለጹት፡፡

በዚህ መሰረት በተለያዩ ዘርፎች ለሚሰማሩ ባለሃብቶች ከ2 ሺህ ሄክታር በላይ በላይ ስፋት ያለው መሬት ማዘጋጀቱን ጠቁመዋል፡፡

ቦታው በጨርቃ ጨርቅ፣ በምግብና መጠጥ፣ በእንጨት እና ብረታ ብረት ስራ እንዲሁም በኬሚካል ዘርፎች ላይ ለሚሰማሩ አልሚዎች የቀረበ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም ቀጠናውን ለኢንቨስትመን ምቹ ለማድረግ አስፈላጊ የሚባሉ የኤሌክትሪክ፣ የውሃ እና መሰል መሰረት ልማቶች መሟላታቸውን ጠቅሰዋል።

ባለሃብቶች ለሚያቀርቧቸው መሰረዊ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠትም ግብረ ሃይል መቋቋሙን ነው ምክትል ከንቲባው ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የተናገሩት፡፡

በኢንቨስትመንት ዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመለየት እና በቀጣይ ዘላቂ መፍትሄ ለማበጀትም በከተማዋ ከሚገኙ የፋብሪካ ባለቤቶች ፣ ከሚመለከታቸው አካላት እና ፍላጎት ካላቸው ባለሃብቶች ጋር ምክክር መደረጉን ጠቁመዋል።

አሁን ላይም በርካታ የውጭ እና የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች በከተዋማ ለኢንቨስትመንት የተመረጡ ቦታዎችን እየጎበኙ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ስለሆነም ባለሃብቶች በደብረ ብርሃን እና አካባቢዋ ያለውን ምቹ የኢንቨስትመንት ሁኔታ በመመልከት መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ አቶ በድሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

Exit mobile version