አዲስ አበባ፣ ጥር 25፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ጃፓናዊው ካዙዮሺ ሚዩራ ጠንካራ የአካል ብቃትን በሚጠይቀው የእግር ኳስ ስፖርት በ55 አመቱ መጫወቱን ቀጥሏል።
ጃፓናዊው ጎልማሳ በዚህ እድሜው በፖርቹጋል ሁለተኛ ዲቪዚዮን ለሚገኘው ኦሊቬረንሴ ክለብ በውሰት ለመጫዎት ፊርማውን አኑሯል።
ሚዩራ ከጃፓኑ ጀ ሊግ የእግር ኳስ ክለብ ዮኮሃማ ነበር ወደ ፖርቹጋሉ ሁለተኛ ዲቪዚዮን ክለብ ኦሊቬረንሴ የፈረመው፡፡
ቀደም ሲል በብራዚል፣ ጃፓን፣ ጣሊያን፣ ክሮሺያ እና አውስትራሊያ ሊጎች መጫዎት የቻለው ሚዩራ ወደ ፖርቹጋል ሊግ መዘዋወሩን ተከትሎ በጠቃላይ በስድስት ሀገራት ሊጎች መጫዎት ችሏል፡፡
ከዝውውሩ በኋላ ባደረገው ንግግርም “ይህ ለእኔ አዲስ ቦታ ቢሆንም ችሎታየን ለሁሉም ለማሳየት ጠንክሬ እሰራለሁ” ብሏል።
ቀደም ሲል ተጫዋቹ እስከ 60 አመቱ ድረስ ለመጫወት እቅድ አለኝ ሲል መናገሩን ቢቢሲ ስፖርት ዘግቧል፡፡
ሚዩራ ባለፈው የውድድር ዓመት በሱዙካ ፖይንት ጌተርስ ክለብ በውሰት ያሳለፈ ሲሆን 18 ጨዋታዎችን አድርጎ ሁለት ግቦችን ማስቆጠር ችሏል፡፡
በ1986 በብራዚሉ ክለብ ሳንቶስ የእግር ኳስ ህይወቱን የጀመረው ሚዩራ በጃፓን ፕሮፌሽናል ሊግ በ2017 ባስቆጠራት ጎል በ50 አመቱ ጎል ያስቆጠረ ብቸኛ ተጫዋች ክብረ ወሰንን ይዞ ቆይቷል፡፡
በጃፓናውያን “ኪንግ ካዙ”በመባል የሚወደሰው ካዙዮሺ ሚዩራ በጃፓን ከሚወደዱ ስፖርተኞች መካከል ቀዳሚ መሆን ሲችል ለጃፓን 89 ጊዜ በመሰለፍ 55 ጎሎችን አስቆጥሯል።