አዲስ አበባ፣ ጥር 25፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ብሪታኒያ ከአውሮፓ ህብረት በመውጣቷ በዓመት ከ124 ቢሊየን ዶላር በላይ እያሳጣት መሆኑን የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ገለጹ፡፡
ብሪታኒያ ከአውሮፓ ህብረት መውጣቷን ተከትሎ በየዓመቱ በቢሊየኖች የሚቆጠር ገንዘብ እያጣች መሆኑን የብሉምበርግ ኢኮኖሚክስ ሪፖርት ያመላክታል።
ሪፖርቱ እንዳመለከተው ፥ የብሪታንያ ኢኮኖሚ በአሁኑ ጊዜ ሀገሪቱ በህብረቱ ውስጥ ብትቆይ ይኖራት ከነበረው በአራት በመቶ ያነሰ ነው።
በ2020 ከአውሮፓ ህብረት ከወጣች በኋላ በዓመት 100 ቢሊየን ፓውንድ (124 ቢሊየን ዶላር) እያጣች መሆኑንም ሪፖርቱ የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎችን ዋቢ አድርጎ ባወጣው ሪፖርቱ አመላክቷል።
የኢኮኖሚ ተንታኞቹ ከ2016 የብሪታኒያ ከህብረቱ ለመነጠል ያለመ ህዝበ ውሳኔ በኋላ የእንግሊዝ ኢኮኖሚ ከቡድን ሰባት አባል የተለየ ነው ይላሉ።
ይህ የተከሰተው ከነጠላ ገበያ ውጭ ስለሚኖራቸው የወደፊት ዕጣ እርግጠኛ ያልሆኑ ኩባንያዎች ወጪን በተመለከተ ከፍተኛ ጥንቃቄ በማድረጋቸው ነው ይላሉ የዘርፉ ባለሙያዎች፡፡
በዚህም በአሁኑ ወቅት የብሪታኒያ የንግድ ኢንቨስትመንት ጠቅላላ እድገት 9 በመቶ ሲሆን ፥ የቡድን ሰባት አባል ሀገራት ደግሞ 13 በመቶ መሆኑን በማነጻጸር ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም በብሪታንያ ያጋጠመው የሰራተኞች እጥረት ከአውሮፓ ህብረት ጋር የፈጸመችው ፍቺ ምክንያት መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፥ ይህም በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ነው የሚገልጹት።
የጉልበት ሰራተኞች እጥረት በአጭር ጊዜ ውስጥ የዋጋ ግሽበትን በማምጣት የኢኮኖሚ እድገትን ይገድባል ማለታቸውን አር ቲ ዘግቧል።