አዲስ አበባ ፣ ጥር 22 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በውጭ ምንዛሬ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለሚያመርቱ ባለሃባቶች እና ተቋማት አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግ የኢትዮጵያ ኢንተርራይዝ ልማት አስታወቀ፡፡
የኢንተርፕራይዙ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዱልፈታ የሱፍ እንደገለጹት÷ተቋማት የውጭ ምንዛሬ የሚያስቀሩ ምርቶችን በሀገር ወስጥ እንዲያመርቱ ለማድረግ በርካታ ፕሮግራሞች ተቀርጸው በቅንጅት እየተሰራ ነው፡፡
ባለፉት ስድስት ወራትም በተለያዩ ዘርፎች በተኪ ምርቶች ላይ የሚሰማሩ አነስተኛ ፣መካከለኛ እና ከፍተኛ ኢንተርፕራይዞች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን አንስተዋል፡፡
በእነዚህ ኢንተርፕራይዞችም ከ212 ሚሊየን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ማዳን መቻሉን የገለጹት አቶ አብዱልፈታ÷ወደ ውጪ ከተላኩ ምርቶችም 15 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል ብለዋል፡፡
በቀጣይም የኤክስፖርት አቅምን ለማሳደግ፣ ገቢ ምርቶችን ለመቀነስ እና በቂ የሥራ እድል ለመፍጠር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር ይሰራል ነው ያሉት፡፡
በተለይም በውጭ ምንዛሬ የሚገቡ ምርቶችን ለሚያመርቱ ተቋማት ከዓለም ባንክና ሌሎች አጋር አካላት ጋር ብድር ማመቻቸትን ጨምሮ ሌሎች መሰረታዊ ድጋፎች የሚደረጉ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም የአቅም ግንባታ፣ የስራ ክህሎት ስልጠና፣ የቴክኒክ እና ሌሎች አስፈላጊ ድጋፎች እንደሚደረጉ ተናግረዋል፡፡
ስለሆነም ባለሃብቶችና ተቋማት ወደ በተኪ ምርቶች ላይ ትኩረት አድርገው እንዲሰሩና የቀረበውን መልካም እድል እንዲጠቀሙ ነው አቶ አብዱልፈታ ጥሪ ያቀረቡት፡፡ በመላኩ ገድፍ