አዲስ አበባ፣ ጥር 22፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ አገኘሁ ተሻገር በኢትዮጵያ ከሩሲያ አምባሳደር ኢቭጌኒ ተርኪሂን ጋር ተወያይተዋል፡፡
በኢትዮጵያና ሩሲያ መካከል በተለያዩ ዘርፎች ያለውን አዎንታዊ ትብብር አጠናክሮ ማስቀጠል አስፈላጊ መሆኑን በውይይታቸው ወቅት ገልጸዋል፡፡
በውይይታቸውም አፈጉባዔ አገኘሁ ተሻገር ኢትዮጵያ ለግጭት አፈታት ተግባራዊነት እየሠራች መሆኑን ጠቅሰው በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ተከስቶ በሠላም የተቋጨው ግጭት የዚህ ተግባራዊነት ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ የጦር መሳሪያ ድምፅ የማይሰማበትና ዘላቂ ሰላም በፅኑ መሰረት ላይ እንዲተከል ሰፋፊ ስራዎች እየተከወኑ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የሩሲያ አምባሳደር ኢቭጌኒ ተርኪሂን በበኩላቸው ሩሲያ እንደትናንቱ ሁሉ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት ይበልጥ አጠናክራ መቀጠል እንደምትፈልግ ገልጸዋል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤትና በሩሲያ የላይኛው ምክር ቤት ማለትም የፌዴሬሸን ምክር ቤት መካከል ያለው መልካም ትብብር ወደላቀ ደረጃ መሸጋገር እንዳለበት ተጠቁሟል፡፡
ለትብብሩ መጠንከር ይረዳ ዘንድ በቅርቡ በሞስኮ በሚካሄደው የሩሲያና አፍሪካ ምክር ቤቶች ጉባዔ ላይ እንዲሳተፉ አምባሳደሩ ከሩሲያ ፌዴሬሽን የተላከውን የጥሪ ደብዳቤ ለአፈጉባዔው ማስረከባቸውን ከፌዴሬሽን ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡