ዓለምአቀፋዊ ዜና

ቻይና የሠራችው “ሲ 919” አውሮፕላን የመጀመሪያ መደበኛ በረራውን በስኬት አከናወነ

By Alemayehu Geremew

January 29, 2023

አዲስ አበባ፣ ጥር 21፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ቻይና በራስ አቅም የሠራችው “ሲ 919” የመንገደኞች አውሮፕላን ከሙከራ በኋላ ትናንት የመጀመሪያ መደበኛው በረራውን በስኬት አከናውኗል፡፡

አውሮፕላኑ በፈረንጆቹ ታኅሣሥ 26 ቀን 2022 የ100 ሰዓታት የሙከራ በረራ ማካሄዱን አስታውሶ ሲጂቲ ኤን ዘግቧል፡፡

ንብረትነቱ የቻይና ምሥራቃዊ ዓየር መንገድ የሆነው አውሮፕላኑ÷ ከሻንጋይ ሆንግኪያኦ አውሮፕላን ማረፊያ ተነሰቶ ናንቻንግ ቻንቤይ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ያደረገው በረራ በስኬት መጠናቀቁ ተነግሯል።

አውሮፕላኑ በቻይና የንግድ አውሮፕላኖች ማምረቻ ኮርፖሬሽን መሠራቱ ተመልክቷል፡፡

የቻይናው ሲቪል አቪዬሽን አስተዳደር የቻይና ምሥራቃዊ ዓየር መንገድ ግዙፉን አውሮፕላን በስኬት ማብረር ስለመቻሉ ምርመራ ካካሄደ በኋላ÷ የሥራ ፈቃድ እንደሚሠጠው የዓየር መንገዱ የጂያንግዚ ምርት ማዘዣ ማዕከል ዳይሬክተር ው ጂንጁን ተናግረዋል፡፡