ስፓርት

የስፖርቱ ቤተሰብ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽን ለመግታት ለሚደረገው ጥረት ድጋፍ ማድረጉን ቀጥሏል

By Tibebu Kebede

April 06, 2020

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 28 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የስፖርቱ ቤተሰብ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽን ለመግታት ለሚደረገው ጥረት ድጋፍ በማድረግ ላይ ናቸው።

የአዲስ አበባ ወርልድ ቴኳንዶ_ፌዴሬሽንም ዛሬ ለኮሮና ቫይረስ መከላከልና ጥንቃቄ የሚውል የ50 ሺህ ብር ድጋፍ አድርጓል።

ፌዴሬሽኑ የክለብ አሰልጣኞች፣ ስፖርተኞች፣ ባለድርሻ አካላትና አብረውት የሚሰሩ ተቋማትን በማስተባበር በቀጣይ ድጋፎችን ለማከናወን ማቀዱንም አስታውቋል።

ሁሉም የስፖርት ቤተሰብ የሚተላለፉ መልዕክቶችን በመተግበር ራሱን፣ ቤተሰቡንና ማህበረሰቡን ከዚህ ቫይረስ እንዲጠብቅም አሳስቧል።

ድጋፉን የተቀበሉት የአዲስ አበባ ስፖርት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ዳዊት ትርፉ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት የስፖርት ማህበራት ሰፊ እንቅስቃሴ ማድረጋቸውን ጠቁመው፥ የአዲስ አበባ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን ስራ አስፈፃሚ አባላት ወስነው የ50 ሺህ ብር ድጋፍ በማድረጋቸው ምስጋናቸውን አቅርበዋል ።

ምክትል ኮሚሽነሩ በዚሁ ወቅት በቤታቸው ተቀምጠው ያሉ ነዋሪዎች በተለይ በጋራ መኖሪያ ቤቶች የሚኖሩ ሰዎች ሳይወጡ በበረንዳቸው ላይ ወጣ ብለው ርቀታቸውን ጠብቀው ራሳቸውን የሚያነቃቁበት እና ከድብርት የሚላቀቁበት የአካል እንቅስቃሴ ቀለል ባለ ሁኔታ በባለሙያ ድጋፍ እንዲሰሩ መመቻቸቱንና ይህም ነገ በተመረጡ የጋራ መኖሪያ ቤቶች እንደሚጀመር ተናግረዋል ።