ኮሮናቫይረስ

በኮሮና ቫይረስ ተጋላጭ በሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ላይ በስፋት ምርመራ ለማካሄድ እየተሰራ ነው

By Tibebu Kebede

April 06, 2020

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 28 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በኮሮና ቫይረስ ተጋላጭ በሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ላይ በስፋት ምርመራ ለማካሄድ እየተሰራ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ከመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካኝነት ምላሽ ሰጥተዋል።

በምላሻቸውም በስራ ባህሪያቸው ለቫይረሱ ተጋላጭ የሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች ላይ የሚደረገው ምርመራ ተጠናክሮ መቀጠሉን አስረድተዋል።

በተጨማሪም ለቫይረሱ ተጋላጭ የሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች በተለይም ቫይረሱ በተገኘባቸው አካባቢዎች ላይ ምርመራው በስፋት ይካሄዳል ነው ያሉት።

ከዚህ ቀደም በሆስፒታሎች የሚሰጠውን የምርመራ ሂደት አሁን በይበልጥ በማስፋት በጤና ጣቢያዎች ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል።

የህክምና ቁሳቁስና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን ለማሟላት በብሔራዊ ኃብት ማሰባሰብ ግብረ ኃይል በኩል እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፥ ኅብረተሰቡ እያሳየ ያለውን አጋርነት ይበልጥ በማጠናከር ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።