Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ከ4 ሚሊየን ብር በላይ የመዘበረው የባንክ ሒሳብ ሹም በ7 ዓመት ፅኑ እሥራትተቀጣ

አዲስ አበባ፣ ጥር 17፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በ”ኦሮሚያ ባንክ” አወዳይ ቅርጫፍ ከ3 ደንበኞች ሒሳብና ከባንኩ ካዝና ከ4 ሚሊየን ብር በላይ ገንዘብ በመመዝበር በከባድ ዕምነት ማጉደል የሙስና ወንጀል የተከሰሰው የሂሳብ ሹም በሰባት ዓመት ፅኑ እሥራትና በገንዘብ እንዲቀጣ ተወሰነ።

የቅጣት ውሳኔውን የወሰነው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ድሬዳዋ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት ነው።

በፅኑ እሥራትና በገንዘብ ቅጣት እንዲቀጣ የተወሰነበት ተከሳሽ ዲኖ ቶፊቅ ሻፊ ÷የኦሮሚያ ባንክ አወዳይ ቅርጫፍ ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ የሒሳብ ሹም ባለሙያ ሆኖ አገልግሏል።

በተከሳሹ ላይ ሁለት ተደራራቢ ክሶች የቀረቡበት ሲሆን÷ በአንደኛው ክስ የሙስና ወንጀሎችን ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ 881/2007 አንቀጽ 3/1 ድንጋጌን በመለላለፍ ሃላፊነቱን ወደጎን በመተው ከባንኩ አሰራር ውጭ የ 3 ደንበኞችን ሥምና ፊርማ አመሳስሎ በመጠቀም በተለያዩ ቀናቶች በአጠቃላይ 1ሚሊየን 664 ሺህ ብር ከደንበኞች እውቅናውጪ ከሒሳባቸው በመቀነስ ለግል ጥቅሙ አውሏል ተብሎ በከባድ ዕምነት ማጉደል ሙስና ወንጀል ክስ ቀርቦበታል።

በሁለተኛው ክስ ደግሞ ከባንኩ አሰራር ውጪ ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ ቀናቶች ደንበኞች ለባንኩ ገቢ ሳያደርጉ በተለያዩ የገቢ ደረሰኝ በማዘጋጀትና በመጠቀም ገቢ እንዳደረጉ በማስመሰልና 3ሚሊየን 325 ሺህ 869 ብር ከ03 ሳንቲም ከባንኩ ካዝና በመበዝበር በባንኩ ላይ ከፍተኛ ኩዳት በማስከተል የሙስና አዋጅ አንቀጽ 13 ንዑስ ቁጥር 2 ስር ያለውን ድንጋጌ ተላልፏል ተብሎ በታኅሣሥ 12 ቀን በ2013 ዓ.ም ሥራን በማያመች አኳኋን መምራት ሙስና ወንጀል ተከሷል።

ተከሳሹ ክሱ ከደረሰው በኋላ ወንጀሉን አለመፈጸሙን ገልጾ ÷የሰጠውን የዕምነት ክህደት ቃል ተከትሎ ዐቃቢ ኅግ የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን አቅርቦ አሰምቷል።

ፍርድ ቤቱ የዐቃቤ ኅግ ማስረጃን መርምሮ ተከሳሹ በተከሰሰበት ድንጋጌ እንዲከላከል ብይን የተሰጠ ሲሆን÷ ተከሳሹም በተለያዩ ቀናቶች የመከላከያ ማስረጃ አቅርቦ አሰምቷል።

ሆኖም ተከሳሹ ያቀረበው የመከላከያ ማስረጃ በችሎቱ ተመርምሮ ዐቃቢ ኅግ ያቀረበበትን የሰውና የሠነድ ማስረጃ ተከሳሹ በተገቢው ማስተባበል አልቻለም ተብሎ የጥፋተኝነት ፍርድ ተላልፎበታል።

ከዚህም በኋላ ተከሳሹ የቤተሰብ አስተዳዳሪ እና የወንጀል ሪከርድ የሌለበት መሆኑን ጠቅሶ የቅጣት ማቅለያ አስተያየት በፅሑፍ አቅርቧል።

በዐቃቢ ኅግ በኩል ቅጣቱ ከብዶ እንዲጣል የቅጣት ማክበጃ አስተያየት ቀርባል፡፡

ፍርድ ቤቱም የተከሳሹ የቅጣት ማቅለያ በመያዝ እና በዐቃቤ ኅግ በኩል ተከሳሹ የቀደመ የወንጀል ሪከርድ ባለመኖሩ ፍርድ ቤቱ በወንጀለኛ መቅጪያ ሥነ-ሥርዓት ኅግ አንቀጽ 179 እና በቅጣት አወሳሰን መመሪያ ቁጥር 2/2006 አንቀጽ 23 ንዑስ ቁጥር 4 መሠረት ከቅጣት ዕርከን በመውረድ ተከሳሹን በ7 ዓመት ፅኑ እሥራትና በ20 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት እንዲቀጣ ተወስኗል።

በታሪክ አዱኛ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version