ባለፉት 6 ወራት ከ1 ነጥብ 1 ቢሊየን ዶላር በላይ የሚያወጡ ገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካት ተችሏል
አዲስ አበባ፣ ጥር 16፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት 6 ወራት ከ1 ነጥብ 1 ቢሊየን ዶላር በላይ የሚያወጡ በውጭ ምንዛሬ የሚገቡ ምርቶች በሀገር ውስጥ ምርት መተካት መቻሉን የአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡
የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ስለሺ ለማ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት÷አምራች ኢንዱስትሪዎች ተኪ ምርቶችን በጥራትና በብዛት እንዲያመርቱ በቅንጅት እየተሠራ ነው፡፡
በዚህ መሰረትም ኢንዱስትሪዎች በወጪ ንግድ እና በምንዛሬ በሚገቡ ምርቶች ላይ እንዲሰማሩ የሚያስችሉ 28 ጥናት እና ምርምሮች መደረጋቸውን አንስተዋል፡፡
እነዚህ ችግር ፈቺ ጥናት እና ምርምሮችም አምራች ኢንዱስትሪዎች ከተኪ ምርቶች ባለፈ በርካታ ምርቶችን ወደ ውጭ በመላክ የውጪ ምንዛሬ ማስገኘት መቻላቸውን አስረድተዋል፡፡
ባለፉት 6 ወራትም ከአምራች ኢንዱስትሪዎች ወጪ ንግድ 194 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄም ባለፉት 6 ወራት ከ1 ነጥብ 1 ቢሊየን ዶላር በላይ የሚያወጡ ገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት መተካት መቻሉን አንስተዋል፡፡
ውጤቱ አምራች ኢንዱስትሪው አሁን ላይ ተኪ ምርቶችን ማምረት ከሚችለው 53 በመቶ የሚሆነውን ብቻ በመጠቀም የተገኘ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በዚህም ከተያዘው ዕቅድ ከመቶ በመቶ በላይ ማሳካት መቻሉን ጠቁመው÷ በቀጣይ ኢንዱስትሪዎች በተኪ ምርቶች ላይ በስፋት እንዲሰማሩ ይሠራል ብለዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ