Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በአሸባሪው ሸኔ ላይ እየተወሰደ ባለው እርምጃ የፀጥታ ሁኔታው እየተሻሻለ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ጥር 16፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአሸባሪው ሸኔ ላይ በመከላከያ እና በክልሉ ፀጥታ ኃይል እየተወሰደ ባለው እርምጃ የፀጥታ ሁኔታው እየተሻሻለ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ አስታወቀ፡፡

የቢሮው አቶ ኃላፊ ኃይሉ አዱኛ ዛሬ በሰጡት መግለጫ÷ በአሸባሪው ሸኔ ላይ በተወሰደው እርምጃ በቁጥጥሩ ስር የነበሩ አካባቢዎችን ማስለቀቅ ተችሏል ብለዋል።

የክልሉ መንግሥት ሰላምን ለማረጋገጥ ከህብረተሰቡ ጋር እየሠራ መሆኑንም ነው ኃላፊው በመግለጫቸው ያነሱት፡፡

ለዚህም ባለፈው ሣምንት በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ የተመራ ልዑክ በወለጋ ዞኖች ከህብረተሰቡ ጋር ያካሄደው ውይይት ማሳያ ነው ብለዋል።

ከምዕራብ፣ ከምሥራቅ እና ከቄለም ወለጋ ዞኖች ነዋሪዎች ጋር በተደረገው ውይይትም የፀጥታ ጉዳይ ቀዳሚው አጀንዳ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

የዞኖቹ ነዋሪዎች መንግሥት ፀጥታን እንዲያረጋግጥ መጠየቃቸውን እና የበኩላቸውን እንደሚወጡ ማረጋገጣቸውን አቶ ኃይሉ በመግለጫቸው አመላክተዋል፡፡

በተጨማሪም በአሸባሪው ሸኔ የወደሙ መሰረተ ልማቶች እንዲሟሉ እና የሥራ አጥነት ችግር እንዲፈታ ነዋሪዎቹ መጠየቃቸው በመግለጫው ተጠቁሟል፡፡

የክልሉ መንግሥት ለጸጥታ ጉዳይ ቅድሚያ በመስጠት ከነዋሪዎቹ የተነሱትን ጥያቄዎች በሂደት ለመመለስ በትኩረት እንደሚሠራ ተገልጿል፡፡

በደበላ ታደሠ እና አዳነች አበበ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version