Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የከተራ እና ጥምቀት በዓላት በሰላም ተጠናቅቀዋል-የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

አዲስ አበባ፣ ጥር 12፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የከተራ እና ጥምቀት በዓላት በሰላም መጠናቀቃቸውን የኢፌዴሪ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ፡፡
 
መንግስት በዓላቱ በድምቀትና በሰላም እንዲጠናቀቁ ላደረጉ አካላት ሁሉ ምስጋና አቅርቧል፡፡
 
አገልግሎቱ ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ÷በዓላቱ ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ ገጽታቸውን ጠብቀው፤የሕዝብ አብሮነትን አጉልተው በስኬት ተጠናቅቀዋል ብሏል፡፡
 
የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
 
የከተራ እና ጥምቀት በዓላት በሰላም ተጠናቅቀዋል!
 
በዓላቱ በድምቀትና በሰላም እንዲጠናቀቅ ላደረጉ አካላት ሁሉ መንግሥት ምስጋና ያቀርባል፡፡
 
በዓላቱ ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ ገጽታቸውን ጠብቀው፤ የሕዝብ አብሮነትን አጉልተው፤ ኢትዮጵያውያንን ከአንዱ ቦታ ወደ ሌላው ቦታ ስበው ብዙ ሚሊየን ቱሪስቶችን አስተናግደው በስኬት ተጠናቅቀዋል፡፡
 
በዚህም በመላው ኢትዮጵያ አብዛኛዎቹ ታቦታት ወደ መንበሮቻቸው ተመልሰዋል፡፡ላለፉት ሁለት ዓመታት በጦርነት ድባብ ውስጥ የቆዩ አካባቢዎች ሳይቀሩ የዘንድሮን የጥምቀት በዓል በደማቁ አክብረውታል፡፡ በዓላቱ በመተሳሰብ፤በአንድነት እና በእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ ኢትዮጵያዊ ዕሴትን አድምቀው በሰላም ተጠናቅቀዋል፡፡
 
በመላው ኢትዮጵያ ሚሊየኖች በዓሉን ሲያከብሩ የፌደራል እና የክልል የጸጥታ ኃይሎች ደግሞ ለ24 ሰዓታት ያለመታከት የሕዝቡን ሰላም ጠብቀዋል፡፡በአንድ አንድ ቦታዎች የጥፋት ተልእኮን ተቀብለው በዓሉን ለማወክ ፍላጎት የነበራቸው የጥፋት ሃይሎች በተቀናጀ የፀጥታ አካላትና በሕዝቡንቁ ተሳትፎ ከሽፏል፡፡
 
እንደሌላው ጊዜ ሁሉ አሁንም የሰላም ዘብነታቸውን እና የሀገር አለኝታነቸውን በተግባር አስመስክረዋል፤በዓላቱን ለመረበሽ ላሰቡ አካላት መፈናፈኛ አሳጥተው ታላቅ ተጋድሎ ፈጽመዋል፡፡
 
የሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎችም የበዓላቱን ሂደት እየተከታተሉ በማሠራጨት ለበዓሉ በስኬት መጠናቀቅ ጉልህ ሚና ተጫውተዋል፡፡ የሃይማኖት አባቶች በዓላቱን አስመልክተው ያስተላለፏቸው መልዕክቶች፤የሕዝብን አንድነት እና ዘላቂ ሰላማችንን ለማስጠበቅ የማይተካ ሚና ተጫውተዋል፡፡
 
የተለያዩ የእምነት መሪዎችና ተከታዮች በዓላቱ በሰላምና በድምቀት እንዲከበሩ ያሳዩት ተሳትፎ የኢትዮጵያን እውነተኛ መልክ ያሳየ ነው፡፡
 
ስለሆነም መንግሥት የዘንድሮው የከተራ እና የጥምቀት በዓላት በሰላም እና በስኬት እንዲጠናቀቁ ላደረጉ አካላት ሁሉ ምስጋናውን ያቀርባል፡፡
 
ኅብረተሰቡም ከጸጥታ አካላት ጋር በመተባበር በዓላቱ በሰላም እንዲጠናቀቁ ላደረገው አስተዋጽዖ መንግሥት ምስጋናውን እያቀረበ፤ በቀጣይ በሚደረጉ ሀገራዊ ክንውኖችም ከመንግሥት ጋር ተባብሮ የኢትዮጵያን ብልጽግና እንዲያሳካ ጥሪውን ያቀርባል፡፡
 
ጥር 12/2015 ዓ/ም
 
አዲስ አበባ፣
 
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት፣
Exit mobile version