የሀገር ውስጥ ዜና

በመዲናዋ በተለያዩ ምክንያቶች ተቆፍረው የሚተዉ ጉድጓዶች በሰዎች ላይ ጉዳት እያደረሱ ነው – ኮሚሽኑ

By Feven Bishaw

January 20, 2023

 

አዲስ አበባ፣ ጥር 12፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በመዲናዋ በተለያዩ ምክንያቶች ተቆፍረው የሚተዉ ጉድጓዶች በሰዎች ላይ ጉዳት እያደረሱ መሆኑን የአዲስ አበባ እሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ገለፀ፡፡

በኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ንጋቱ ማሞ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደተናገሩት÷ በመዲናዋ ለመሰረተ ልማት ግንባታ ፣ለግንባታ፣ ድንጋይና ሌሎች ማዕድናትን ለማውጣትና ለተለያዩ ምክንያቶች ተቆፍረው የሚተዉ ጉድጓዶች ተበራክተዋል፡፡

በተለይ አንዳንድ ድንጋይ ለማውጣትና ሌሎች ማዕድናትን ለማውጣት ተቆፍረው የሚተዉ ጉድጓዶች ስፋታቸው ከ70 እስከ 100 ሜትር ጥልቀታቸው ደግሞ እስከ 15 ሜትር እንደሚደርስ ገልፀዋል፡፡

እነዚህ ጉድጓዶችም በተለይ በክረምት ወቅት ውሃ ስለሚያቆሩ ህፃናት ለመዋኘትና ለመታጠብ በሚል በመግባት ሕይወታቸውን እንደሚያጡ ነው የተናገሩት፡፡

መሰል ችግሮች በመዲናዋ በሁሉም አካባቢዎች ቢኖሩም በንፋስ ስልክ ላፍቶ፣ የካ እና ቦሌ ክፍለ ከተሞች በርካታ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በዚህም በተያዘው ዓመት በተለያዩ ምክንያቶች ተቆፍረው በሚተዉ ጉድጓዶች ውስጥ በመግባት ሶስት ሰዎች ህይወታቸውን እንዳጡ ጠቁመው፥ ይህ ቁጥር ለኮሚሽኑ ሪፖርት የተደረገ ብቻ በመሆኑ ቁጥሩ ከዚህም ከፍ ሊል እንደሚችል ገምተዋል።

እንዲሁም የሰዎች እንቅስቃሴ ባለበት በተለይ በመሰረተ ልማት አቅራቢዎች ክፍት የሆኑ ጉድጓዶች መኖራቸውንና ሳይከደኑ በርካታ ጊዜያት ሊያስቆጥር እንደሚችሉ ተናግረው ይህም ምሽት ላይ እና ለትራንስፖርት አገልግሎት በሚደረግ እንቅስቃሴ የተለያዩ መጠን ያላቸው ጉዳቶችን እየደረሱ ነው ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ በግለሰብም ሆነ በመንግስት ለግንባታ ስራዎች ተብለው ተቆፍረው የሚተዉ ጉድጓዶች እንዳሉም ገልፀው ፤ በዚህም አንዳንዶቹ ስራው ሲካሄድ በቂ ከለላ እና ጉድጓድ ስለመኖሩ ምልክት እንደማይቀመጥና አደጋዎችም እየተበራከቱ መምጣታቸውን ገልፀዋል፡፡

ይህን የቆየ ችግር ክትትል እያደረገ ለሚመለከተው አካል ቢያሳውቅም ምላሽ ግን እያገኘ አለመሆኑን አንስተዋል፡፡

በዚህም በሃላፊነትና መፍትሄው ላይ መስራት ፣ድንጋይ ለማውጣትም ሆነ ሌሎች ማዕድናትን ለማውጣት ፍቃድ የሚሰጠው አካል አስፈላጊው ክትትል ማድረግ ፣የተቆፈሩ ጉድጓዶች አካባቢ መከለል፣አደጋን ተከላክለው ከሚሰሩ ተቋማት ልምድ መውሰድ ፣ የተቆፈሩ ጉድጓዶችን ተከታትሎ መክደን / መድፈን/ መዝጋት እንደሚገባ መክረዋል፡፡

ህብረተሰቡም የራሱን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባው ነው የተናገሩት፡፡

እንዲሁም በእነዚህ ጉድጓዶች ምክንያት ለሚደርሱ አደጋዎች እና ጉዳቶች ለአደጋው ምክንት የሆነው ተቋም ፣ድርጅት ሆነ ግለሰብ ተጠያቂ ሊሆን እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

በፌቨን ቢሻው