አዲስ አበባ፣ ጥር 11፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) “ሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቶቻችን ይበልጥ እየጎለበቱ የዓለም እንዲሆኑ አንድ መሆንና ሰላም ማስፈን ብቻ ነው የሚያስፈልገን” ሲሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ ተናገሩ።
ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው በኩል ባስተላለፉት መልዕክት፥ “የዛሬው የጥምቀት በዓል በሁሉም ያገራችን ጥግ እጅግ ባማረና ባሸበረቀ አኳኋን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክህነት ህግ፣ እምነትና ቀኖናን መሠረት አድርጎ በደመቀ ሁኔታ ያለምንም ኮሽታ በሰላም ተከብሯል” ብለዋል።
“ይህ የመንግስታችን ፍላጎት በመሆኑ እጅግ አስደስቶናል” ነው ያሉት በመልዕክታቸው።
ለዚህ መንፈሳዊ ስኬት ከሁሉም በላይ በሃላፊነት ስሜት የተንቀሳቀሱ የዕምነቱ ተከታይ ወጣቶች መሆናቸውን ገልፀዋል።
እነዚህ ወጣቶች የዕምነቱን ሰላማዊናት ብቻ ሳይሆን ቤተክህነት ፈጣራን ለዓለም እንደምታበረክት በየአብያተ ክርስቲያኑ ያሳዩት ድንቅ ስራና ለትውልድ ያስተላለፋት መልዕክት የኢትዮጵያውያን የማይነጥፍ የፈጠራ ስራ የሚያሳይ በመሆኑ የሚደነቅ ነው ብለዋል።
በሁሉም አካባቢ ላሉ የፀጥታ መዋቅርና በየደረጃው በማስተባበር ስራ ላይ ለተሰማሩ የአስተዳደር አካላት መንግሥት ልዩ ክብር እንዳለውም ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።
ሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቶቻችን ይበልጥ እየጎለበቱ ፣ የዓለም ይሆናሉ ” ያሉት ሚኒስትሩ፥ “ይህ እውን እንዲሆን አንድ መሆንና ሰላም ማስፈን ብቻ ነው የሚያስፈልገን” ብለዋል።