Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የተለያዩ ክልሎች ለጥምቀት በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

አዲስ አበባ፣ ጥር 10፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የተለያዩ ክልሎች መንግስታት ለጥምቀት በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
 
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስት ለበዓሉ ባስተላለፈው መልዕክት ÷ የጥምቀት በዓል ከኃይማኖታዊ ይዘቱ ባሻገር ማኅበራዊ ግንኙነትን በማጠናከር ረገድ ፋይዳው የጎላ መሆኑን አውስቷል።
 
በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ በአደባባይ ከሚበሩ በዓላት በቀዳሚነት የሚጠቀሰው የጥምቀት በዓል ÷ የተለያዩ ጎብኚዎችን በመሣብ ሀገራችንን ለዓለም በማስተዋወቅ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው ሲልም ገልጿል።
 
የእምነቱ ተከታዮች በዓሉን ሲያከብሩ ኢየሱስ ክርስቶስ በጥምቀቱ ያስተማረውን ትህትናንና መከባበርንና በተግባር በማሣየት መሆን ይገባል ነው ያለው።
 
የሐረሪ ክልላዊ መንግስትም ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች ለከተራና ለጥምቀት በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፏል፡፡
 
ክልሉ በመልዕክቱም ÷ የጥምቀት በዓል ከሃይማኖታዊ በዓልነቱ ባሻገር የሀገሪቱ መልካም ገፅታን ከመገንባትና የቱሪስት ፍሰትን ከማጎልበት አንፃር ጉልህ ሚና እንዳለው አውስቷል፡፡
 
በዓሉ በክልሉ ሲከበርም ሰላምንና አብሮነት በሚያጠናክር እና መከባበርንና መተሳሰብን በሚያጎለብት እንዲሁም ሀገራዊ ገፅታን በሚያሳድግ መልኩ ሊሆን ይገባል ብሏል፡፡
 
ህብረተሰቡ በዓሉን ሲያከብር እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ የመረዳዳት እና የመደጋገፍ ባህሉን በማጠናከር ሊሆን እንደሚገባ ተጠቁሟል፡፡
 
ከዚህ ባለፈም በዓሉ በሠላም ተከብሮ እንዲጠናቀቅ የጸጥታ አካላት ከሚወጡት ኃላፊነት በተጨማሪ የእምነቱ ተከታዮችም የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀርቧል፡፡
Exit mobile version