አዲስ አበባ፣ ጥር 3፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በፍትሕ ሚኒስቴር የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ የነበሩትን ፈይሳ ሹርኬን ጨምሮ በከባድ የሙስና ወንጀል የተከሰሱ ግለሰቦች ላይ የዐቃቤ ሕግን የሰው እና የሠነድ ማስረጃዎች መርምሮ ብይን ለመስጠት ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጠ።
ተከሳሾቹ÷ 1ኛ በፍትሕ ሚኒስቴር ድሬዳዋ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ የነበሩት ፈይሳ ሹርኬ ሳፋርን፣ 2ኛበድሬዳዋ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ዐቃቤ ሕግ የነበሩት ዓለማየሁ ታደሰ ከበደ እና 3ኛ ፍሬው በቀለ ታየ ናቸው።
ተካሳሾቹ÷ የግል ተበዳይ የሆኑት የአረጋይ ግርማይን በድሬደዋ ከተማ ቀበሌ 03 የሚገኝ ከሙስና ወንጀል ምርመራ ጋር በተያያዘ በፍርድቤት እግድ ያለበትን ሆቴላቸውን ለመሸጥ ‘እግዱን እናስነሳልሀለን’ በሚል እና ጉዳዩን ለማስጨረስ 15 ሚሊየን ብር ጉቦ እንዲከፍል መጠየቃቸው ተገልጿል፡፡
ከጠየቁት ውስጥም 7 ነጥብ 8 ሚሊየን ብር በተለያየ ጊዜ በተለያየ የባንክ ሒሳብ ቁጥር ገቢ እንዲደረግላቸው አድርገዋል ተብለው ነው የተከሰሱት።
በግለሰቦቹ ላይ ዐቃቤ ሕግ ሁለት ክሶችን የመሰረተ ሲሆን አንደኛ ክስ ሶስቱንም ተከሳሾች የሚመለከት ሁለተኛው ክስ ደግሞ በአንደኛ ተከሳሽ ላይ ብቻ የተመሰረተ ነው።
የዐቃቤ ሕግ አንደኛ ክስ÷ ተከሳሾቹ የተሰጣቸውን ስልጣን ያለአግባብ በመጠቀም ከግል ተበዳይ አረጋዊ ግርማይ የ 15 ሚሊየን ብር ጉቦ እንዲከፍሉ በመጠየቅ የግል ተበዳዩ የተጠየቁትን ገንዘብ እንዲከፍሉ ለማድረግ የወንጀል ክስ በመመስረት ጫና በመፍጠርና በማግባባት ጉቦ መቀበላቸውን ያስረዳል፡፡
ተከሳሾቹ የግል ተበዳይ 7 ሚሊየን 800 ሺህ ብር ለሦስተኛ ተከሳሽ እንዲከፍሉ በማድረግ ይህን ላደረጉበትም አንደኛ ተከሳሽ 690 ሺህ ብር ሁለተኛ ተከሳሽ ደግሞ 150 ሺህ ብር መቀበላቸውን ነው ክሱ የሚያስረዳው።
በዚህም ሦስቱም ተከሳሾች በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በፈፀሙት በስልጣን ያለአግባብ መጠቀም ከባድ የሙስና ወንጀል ተከሰዋል።
አንደኛ ተከሳሽን ብቻ የሚመለከተው ሁለተኛው ክስ ደግሞ በወንጀል ድርጊት ያገኘውን ገንዘብ÷ ምንጩን፣ ዝውውሩን ወይም የባለቤትነት መብቱን የደበቀ ወይም እንዳይታወቅ ያደረገ የሚል ነው፡፡
በዚህም በፈፀመው በወንጀል ድርጊት የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብ ወንጀል ዐቃቢ ሕግ ከሶታል።
ዐቃቢሕግም የሠነድ ማስረጃዎችን ጨምሮ ሰባት የሰው ምስክሮችን ለፍርድቤቱ አቅርቦ አሰሞቷል።
የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የፀረሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት የዐቃቤ ሕግን የሰው እና የሠነድ ማስረጃዎች መርምሮ ብይን ለመስጠት ለጥር 19 ቀን 2015 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
በዙፋን ካሳሁን