አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 25 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን ሳይመዘገቡና የብቃት ማረጋገጫ ፍቃድ ሳያገኙ የተለያዩ ግለሰቦችና ተቋማት በህገ ወጥ መልኩ የእጅ ንጽህና መጠበቂያ (Hand sanitizers) ነው በማለት አምርተው ገበያ ላይ እያቀረቡ በመሆናቸው ህብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ጠየቀ።
ባለስልጣኑ በአዋጅ በተሰጠው ስልጣንና ኃላፊነት የምግብና መድኃኒት አስመጪዎች፣ አከፋፋዮችና አምራች ድርጅቶች የብቃት ማረጋገጫ ፍቃድ እንደሚሰጥ ይታወቃል።
በአሁኑ ወቅት የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚያስፈልጉ የእጅ ንጽህና መጠበቂያ ምርቶች በህጋዊ መንገድ በስፋት ተመርተው ገበያ ላይ እንዲቀርቡ ጊዜያዊ ፍቃድ በመስጠት ላይ ይገኛል።
ይሁን እንጅ በተደረገው የገበያ ጥናትና ከህብረተሰቡ በደረሰ ጥቆማ መሰረት በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ሳይመዘገቡና የብቃት ማረጋገጫ ፍቃድ ሳያገኙ የተለያዩ ግለሰቦችና ተቋማት በህገ ወጥ መልኩ የእጅ ንጽህና መጠበቂያ (Hand sanitizers) አምርተው ገበያ ላይ እያቀረቡ መሆናቸውን አስታውቋል።
በመሆኑም ከዚህ በታች የተዘረዘሩት የእጅ ንጽህና መጠበቂያዎች በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ያልተመዘገቡና የብቃት ማረጋገጫ ፍቃድ ያላገኙ እንዲሁም ጥራታቸውና ደህንነታቸው ያልተረጋገጡ በመሆናቸው ከገበያ እንዲሰበሰቡና ህብረተሰቡ እንዳይጠቀማቸው አሳስቧል።
Mela Sanitizer
Narobi Sanitizer
Habesha Sanitizer
FOM Sanitizer
GST Sanitizer
Silva Sanitizer
Yero Hand Sanitizer
Adey Hand Sanitizer
Abyssinia Hand Sanitizer
TAFF አልኮል
መሆናቸውን በማሳወቅ ህብረተሰቡ ጥንቃቄ በማድረግ መሰል ምርቶች ሲያገኝ በአቅራቢያው ለሚገኝ የጤና ተቆጣጣሪ፣ ለፖሊስ አካላት ወይም በፌደራል ደረጃ ለባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በነጻ የስልክ መስመር በ8482 በመጠቆም እንዲያሳውቅም ጠይቋል።