ቢዝነስ

ዳሸን ባንክ “ዱቤ አለ” የተሰኘ የዱቤ ግብይት አገልግሎት መስጠት ጀመረ

By Amele Demsew

January 10, 2023

አዲስ አበባ፣ ጥር 2፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ዳሸን ባንክ “ዱቤ አለ” የተሰኘ በቴክኖሎጂ የታገዘ የዱቤ ግብይት አገልግሎት አስተዋወቀ፡፡

አገልግሎቱ የቆየውን የማህበረሰብ የዱቤ ግብይት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በማገዝ ሸማቾች በዱቤ በፈለጉት ጊዜ ያሻቸውን ገዝተው ቆይተው መክፈል የሚያስችላቸው ነው ተብሏል።

አገልግሎቱን ዳሸን ባንክ ከኤግል ላየን ቴክኖሎጂ እና ከተለያዩ የንግድ ተቋማት ጋር በመተባበር ህብረተሰቡ ቋሚና አላቂ ዕቃዎችን በ3 ፣ በ6 እና በ12 ወር በሚመለስ ዱቤ በወለድና ያለወለድ መግዛት የሚያስችል አማራጭ እንደሆነም ነው የተገለጸው፡፡

የዳሽን ባንክ ዋና ስራ አስፈጻሚ አስፋው አለሙ በማስጀመሪያ ስነ ስረአቱ ላይ እንዳሉት፥ አገልግሎቱ የማህበረሰቡን የኑሮ ጫና ከመቀነስ ባለፈ የንግዱ ማህበረሰብ ሽያጭ እንዲያድግ ብሎም ኢኮኖሚው እንዲነቃቃ ጉልህ ድርሻ ይኖረዋል፡፡

የምርትና አገልግሎት አቅራቢዎች ለደንበኞቻቸው እጅግ አመቺ የሆነ የዱቤ አገልግሎት በማቅረብ ተመራጭነታቸውን ማሳደግ ይችላሉም ብለዋል።

ባንኩ አዳዲስ አገልግሎቶችን በማስተዋወቅ አሞሌ በተሰኘው የዲጂታል ባንክ አገልግሎቱ ሰፊውን የማህበረሰብ ክፍል ተደራሽ ያደረገ ሲሆን በቅርቡም ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመተባበር አነስተኛ ቁጠባና ብድር መጀመሩ ይታወሳል፡፡

በቤቴልሄም መኳንንት