Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በበዓል ሰሞን ሕብረተሰቡ በቴክኖሎጂ ከታገዘ የማጭበርበሪያ ስልት ራሱን እንዲጠብቅ ፖሊስ አሳሰበ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 26፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ሕብረተሰቡ ባልተወዳደረበት እና ባልተሳተፈበት ሁኔታ ሽልማት (ሥጦታ) ደርሶሃል ከሚሉ አጭበርባሪዎች እራሱን እንዲጠብቅ የፌዴራል ፖሊስ አሳሰበ።

በተለያዩ አካባቢዎች የማጭበርበር ወንጀሉ ቢኖርም በተለይም ከአዲስ አበባ በርከት እንደሚልና በጊዜ ረገድም በበዓል ሰሞን እንደሚበዛ ተገልጿል፡፡

በኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ ጀይላን አብዲ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት ፥ ሕብረተሰቡ ባልተወዳደረበትና ባልተሳተፈበት ሁኔታ “ሽልማት (ሥጦታ) ደርሷቹሃል፤ ሥጦታችሁን ለመውሰድም የሥጦታ ማስፈጸሚያ ገንዘብ ክፈሉ” ከሚሉ አጭበርባሪዎች እራሱን ሊጠብቅ ይገባል፡፡

እንደዚህ ዓይነት ማጭበርበሮች ሕብረተሰቡን ለማሕበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና የጤና ዕክሎች እየዳረጉት መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡

ሕብረተሰቡም መሰል ማታለያዎች ሲደርሱት ለመገናኛ ብዙኃን እና ለፖሊስ ጥቆማ መስጠት እንዲሁም ሽልማቱን ሰጠ ከተባለው ተቋም ማረጋገጥ ይገባዋል ብለዋል፡፡

የዘረፋ ዘዴው ከጊዜው ጋር እየተለዋወጠ በቴክኖሎጂ እየተደገፈ መምጣቱን ጠቁመው፥ ሕብረተሰቡ ከእነዚህ አጭበርባሪዎች ለመቆጠብ መፍትሔው በእጁ ላይ መሆኑን ተገንዝቦ ክፍያ ከመፈጸሙ ወይም የትኛውንም ሂደት ከመጀመሩ በፊት ሊያስተውል እንደሚገባ አብራርተዋል፡፡

አንዳንድ ሰዎች ክፍያውን ሳይፈጽሙ ለፖሊስ በሰጡት ጥቆማ ሀብታቸውን ከብክነት መታደግ መቻሉንም ነው ኃላፊው የገለጹት፡፡

ጉዳቱ ከደረሰ በኋላ ወንጀለኞችን ለመያዝ የሚደረገው የክትትል ሥራ እንዲቀል ሕብረተሰቡ ጥቆማ እንዲሰጥ ተጠይቋል፡፡

አጭበርባሪዎቹ የሚኖሩበት እና መታወቂያቸው ላይ ያለው መረጃ የተለያየ በመሆኑ ፖሊስ የሚያደርገውን ክትትል ውስብስብ እንዳደረገው በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡

ሕብረተሰቡ እንደዚህ ዓይነት የማጭበርበር ሁኔታ ሲያጋጥመው በ 01155386040 እንዲሁም በነጻ የስልክ መስመሮች 987 እና 816 ለፌዴራል ፖሊስ በተጨማሪም በ 991 ለአዲስ አበባ ፖሊስ ማሳወቅ እንደሚችል ተጠቁሟል፡፡

በዮሐንስ ደርበው

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version