Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ሀዋሳና ጎንደርን ጨምሮ ከተሞች የኮሮናቫይረስን ለመከላከል የተለያዩ ክልከላዎችንና ውሳኔዎችን እያሳለፉ ነው

አዲስ አበባ፣መጋቢት 24፣2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ሀዋሳ እና ጎንደርን ጨምሮ ሎሌች ከተሞች የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ስርጭትን ለመከላከል የተለያዩ ክልከላዎችንና ውሳኔዎችን እያሳለፉ ነው።

በሀዋሳ ከተማ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ስርጭት ለመከላከል ተጨማሪ ክልከላዎች መጣላቸውን የከተማዋ ምክትል ከንቲባ አቶ ጥራቱ በየነ ገልፀዋል።

የከተማ አስተዳደር ከዚህ ቀደም ከተጣሉ ክልከላዎች በተጨማሪ የአገልግሎት፣ የንግድ እና የማህበራዊ ዘርፎች ላይ እገዳ መጣሉን አስታውቀዋል።

በዚህም መሰረት ከዛሬ 6 ሰዓት ጀምሮ የባለ ሁለት እግር ተሽከርካሪዎች በከተማዋ እንዳይንቀሳቀሱ መከልከሉ ተገልጿል።

እንዲሁም ማንኛውም የመጠጥ ቤት ከምሽቱ 3:00 በኋላ አገልግሎት እንዳይሰጥም መከልከሉን የገለፁ ሲሆን፥ የጭፈራ ቤቶችን በተመለከተ ከዚህ ቀደም እገዳ የተጣለ ቢሆንም አንዳንድ ቤቶች በቸልተኝነት አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙ መሆኑ በመታወቁ ከዛሬ ጀምር ጥብቅ ቁጥጥር እና እርምጃ የሚወሰድ አስታውቀዋል።

በከተማዋ ሀሙስና ሰኞ መደበኛ አገልግሎት እየሰጡ ያሉ የገበያ ስፍራዎች በርካታ ሰዎች የሚገበያዩበት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ህብረተሰቡ ከእነዚህ ውጭ ባሉ ቀናት እንዲጠቀም አስገንዝበዋል።

ሰርግ እና ልዩ ዝግጅቶችን በተመለከተ በአነስተኛ የህዝብ ቁጥር ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታን ህብረተሰቡ እንዲያከናውንም አቶ ጥራቱ መክረዋል።

በጎንደር ከተማም ሚኒ ባስ ፣ ባለ ሶስት እግር ተሽከርካሪ (ባጃጅ) ፣ጋሪና ምግብ ነክ ያልሆኑ የንግድ ተቋማት ከመጋቢት 26 2012 ዓ.ም ጅምሮ አገልግሎት እንዳይሰጡ መከልከሉን የከተማዋ የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ኮማንድ ፖስት አስታውቋል።

የከተማ አስተዳደሩ የኮማንድ ፖስቱ ሰብሳቢና ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ኢንጀነር ማስተዋል ስዩም እንደገለፁት፥ በከተማዋ ከመጋቢት 26 ቀን 2012 ከጧቱ 12 ስዓት ጀምሮ ለቀጣይ 14 ቀናት ክልከላው ተግባራዊ እንደሚሆን ጠቅሰዋል።

ስራ እንዲቀጥሉ የተፈቀደላቸው የንግድ ድርጅቶች ደግሞ ወፍጮ ቤቶች፣ ፈርማሲዎች ፣ክሊኒኮች ዳቦ ቤቶች የእህል መጋዝኖች፣ ምግብ ቤቶችና ሆቴሎች ሲሆኑ፥ ፈቃድ የተሰጣቸው ምግብ ቤቶችና ሆቴሎች 50 በመቶ የመቀመጫ ወንበር በመቀነስ እንዲሰሩ አቅጣጫ መቀመጡን ጠቅሰዋል።

የበድሬዳዋ ከተማ አስተዳደርም የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን በመግለፅ፤ በዛሬው እለትም በከተማዋ ከማዳው ጀምሮ የፀረ ተዋህስያን ኬሚካል ርጭት አካሂዷል።

በተመሳሳይ የሀረሪ ክልልም ከኮሮናቫይረስን ለመከላከል ከዚህ ቀደም ካሳለፈው ውሳኔ በተጨማሪ በዛሬው እለት በሐረር ከተማ ዋና ዋና መንገዶች የፀረ ተህዋህሲያን ኬሚካል ርጭት ማካሄዱን አስታውቋል።

Exit mobile version