የሀገር ውስጥ ዜና

የሰላም ስምምነቱን የሚቆጣጠር፣ የሚያረጋግጥና የሚያስከብር የተልዕኮ ቡድን ተቋቋመ

By Meseret Awoke

December 29, 2022

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 20፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአፍሪካ ሕብረት ስር የሰላም ስምምነቱን የሚቆጣጠር፣ የሚያረጋግጥና የሚያስከብር የተልዕኮ ቡድን ተቋቋመ።

በአፍሪካ ህብረት ስር የሰላም ስምምነቱን የሚቆጣጠር፣ የሚያረጋግጥና የሚያስከበር የተልዕኮ ቡድኑ ሦስት አባላት ያሉት ሲሆን ፥ በሰላም ስምምነቱ መሰረት የሲቪልና ወታደራዊ ስምምነቱን አፈፃፀም ይከታተላል ተብሏል።

ሜጀር ጄነራል ራዲና ስቴፈን ከኬንያ፣ ኮሎኔል ሩፋይ ኡመር ማይሪጋ ከናይጄሪያ እንዲሁም ኮሎኔል ቴፎ ሰኮል ከደቡብ አፍሪካ የተልዕኮ ቡድኑ አባላት ሆነው መሰየማቸውም ነው የተገለጸው።

አባላቱ ዛሬ የፌደራል ፖሊስ በመቀሌ ከተማ ያሉ የመንግስት ተቋማትን የማረካከብ ሂደትን ማስፈጸማቸው ተነግሯል።

በዚህ ወቅት የተልዕኮ ቡድኑ ኃላፊ ሜጀር ጄነራል ራዲና ስቴፈን ፥ የሰላም ስምምነቱን አፈፃፀም ለመረዳት ጠቃሚ መንገድ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በተሰጠን ተልዕኮ መሰረት አፈፃፀሙን እየተከታተልን እንቆጣጠራለን፣ እናረጋግጣለን፣ ውጤቱንም በአፍሪካ ህብረት ስር ለተቋቋመው ኮሚቴ እናሳውቃለንም ነው ያሉት።