የሀገር ውስጥ ዜና

የብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ 1ኛ መደበኛ ጉባዔ ከታኅሣሥ 21 ጀምሮ ይካሔዳል

By ዮሐንስ ደርበው

December 28, 2022

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 19፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ አንደኛ መደበኛ ጉባዔውን ከታኅሣሥ 21 እስከ 25 ቀን 2015 ዓ.ም በአዳማ ከተማ ያካሂዳል፡፡

ለአምስት ቀናት የሚቆየው ጉባዔው “ለኢትዮጵያና አፍሪካዊ ብልጽግና የሚተጋ ወጣት” በሚል መሪ ሐሳብ ነው የሚካሔደው፡፡

የሊጉ ፕሬዚዳንት አስፋው ተክሌ በሰጡት መግለጫ ጉባዔው÷ የተከናወኑ ተግባራትን እንደሚገመግምና የቀጣይ ዓመት ጉዞን ጨምሮ የሊጉን መተዳደሪያ ደንብ ማሻሻል እና ማፅደቅ ላይ ይመክራል፡፡

በተጨማሪም የወጣቶች ማትጊያ ሰነድ ማፅደቅ፣ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ፣ ፕሬዚዳንትና የሌሎችም አካላት ምርጫ የሚሉ ጉዳዮች በአጀንዳነት ይቀርባሉ ብለዋል፡፡

የሊጉ ምክትል ፕሬዚዳንት አክሊሉ ታደሰ በጉባዔው ላይ÷ በሁሉም ዘርፍ ውጤታማ የሆኑ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ በተቋማት፣ በዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች የሚገኙ ወጣቶችን ጨምሮ ሌሎችም እንደሚሳተፉ ጠቁመዋል፡፡

በሳሙኤል ወርቃየሁ