የሀገር ውስጥ ዜና

በጤናው ዘርፍ ህብረተሰቡን ለማገልገል ከዚህ የበለጠ መስራት ያስፈልጋል – ዶ/ር ይልቃል ከፋለ

By Meseret Awoke

December 27, 2022

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 18፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በጤናው ዘርፍ ተደራሽነትን ለማረጋገጥና ህብረተሰቡን ለማገልገል የተደረገው ጥረት አበረታች ቢሆንም ከዚህ የበለጠ መስራት ያስፈልጋል ሲሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ ገለጹ።

“አሳታፊ የጤና አገልግሎት ለወረዳ ትራንስፎርሜሽን ተፈፃሚነት” በሚል ሃሳብ የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ በባህርዳር ከተማ ውይይት እየተደረገ ነው።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ በዚህ ወቅት እንደገለጹት ፥ የሀገራችንን የብልፅግና ጉዞ ለማፋጠን ጤናማ ህብረተሰብ መፍጠር የግድ ይላል ።

እስካሁን በጤናው ዘርፍ ተደራሽነትን ለማረጋገጥና ህብረተሰቡን ለማገልገል የተደረገው ጥረት አበረታች ቢሆንም ከዚህ የበለጠ መስራት ያስፈልጋል ነው ያሉት።

የጤና መድህን ጤናን ለሁሉም ተደራሽ የማድረግ ሀሳብ ሲሆን ፥ ለዚህ ደግሞ ሁሉም ቤተሰብ አባል መሆን ይጠበቅበታልም ብለዋል፡፡

በዚህም ሁሉም ዜጋ የጤና መድህን ሽፋን እንዲያገኝ መስራት እንደሚገባ ተናግረው ፥ የጤና አገልግሎት አሰጣጥ የህብረተሰቡን እርካታ በሚያሟላ መንገድ ሊሆን እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር መልካሙ አብቴ በበኩላቸው ፥ ተቋሙ በጦርነቱ የተጎዱ ዜጎችን የህክምና ድጋፍ እንዲያገኙና ኮቪድ-19ን በመከላከል ልዩ ልዩ አገልግሎቶች በመስጠት ውጤት መገኘቱን አንስተዋል።

ከበፊቱ በተሻለ ንቅናቄ በማድረግም 14 ነጥብ 2 ሚሊየን ህዝብ የማህበረሰብ ጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አስረድተዋል።

በመርሐ ግብሩ የክልሉ የ2014 ዓ.ም የጤና መድህን አፈፃፀምና የ2015 ዓ.ም እቅድ ላይ ውይይት የሚካሄድ ሲሆን ፥ በዘርፉ የአገልግሎት አሰጣጥ ሂደትም ምክክር ይደረጋል።

በሙሉጌታ ደሴ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/ ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!