አዲስ አበባ ፣ ታኅሣሥ 17 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአደረጃጀት ጥያቄዎች የህዝብን እና የሀገርን ዘላቂ ጥቅም በሚያረጋግጥ መንገድ ምላሽ እያገኙ ነው ሲሉ የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እርስቱ ይርዳው ገለጹ፡፡
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምስረታና ነባሩን በአዲስ የማደራጀት ማስፈፀሚያ ፕሮጀክት ፅህፈት ቤት የክልሉ አብይ ኮሚቴ በተገኘበት የአፈፃፀም ሪፖርቱን በዲላ ከተማ አስገምግሟል።
የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እርስቱ ይርዳው በዚሁ ጊዜ እንደገለፁት የክልሉ ህዝብ ለበርካታ ዘመናት ከአደረጃጀት ጋር ተያይዞ ጥያቄ ሲያነሳ ቆይቷል።
ከአደረጃጀት ጋር ተያይዞ የሚነሱ የጥያቄዎች የመልካም አስተዳደር ችግር ከመሆንም አልፎ የግጭት መንስኤ ቆይቷልም ነው ያሉት፡፡
የአደረጃጀት ጥያቄው በተናጠል የተያዙ ሀሳቦችን በማቅረብ የበለጠ ተጠቃሚ በሚያደርግ መንገድ መቃኘቱ እና ዘላቂ ጥቅም በሚያስገኝ አኳያ ከስምምነት መደረሱን አቶ እርስቱ ጠቅሰዋል።
ስምምነቱም ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ቀርቦ ውሳኔ መሰጠቱንም ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል።
በክልሉ አሁን ያሉ ህዝቦች ሁለት ክልል ሆነው እራሳቸውን ችለው የሚያደራጁበት ሁኔታ እንዲፈጠር የመነሻ ውሳኔ መሰጠቱንም ተናግረዋል፡፡
የአንዱ ክልል ህዝበ ውሳኔ እየተካሄደ መሆኑን የተናገሩት ርዕሰ መስተዳድሩ ቀሪው የህዝቦችን ጥያቄ ምላሽ መስጠት በሚያስችል መንድ እራሱን መልሶ እንዲያደራጅ አቅጣጫ መቀመጡንም ነው የጠቆሙት፡፡
በፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ መሰረት የህዝበ ውሳኔውንና ህዝበ ውሳኔውን ተከትሎ ለሚመጣው ውጤት የአደረጃጀት ስራው በደንብ እንዲመራ ፕሮጀክት ፅህፈት ቤት መቋቋሙንም አስረድተዋል።
ህዝበ ውሳኔውን ተከትሎ ለሚመጡ ውሳኔዎች ከወዲሁ ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ከክልሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል::ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-