አዲስ አበባ፣ መጋቢት 23፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ተጨማሪ ሶስት ሰዎች ባለፉት 24 ሠዓታት መገኘታቸውን የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ አስታወቁ።
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ባለፉት 24 ሰዓት ውስጥ 68 የላቦራቶሪ ምርመራ አካሂዶ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ተጨማሪ ሶስት ሰዎች መኖራቸውን አረጋግጧል፡፡
ኢንስቲትዩቱ ይህ መረጃ እስከ ተዘጋጀበት ሰዓት ድረስ በአጠቃላይ 1 ሺህ 83 የላቦራቶሪ ምርመራ ማድረጉ ነው የተገለፀው።
በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጡት ሶስት ግለሰቦች ሁሉም ኢትዮጵያውያን ናቸው ተብሏል።
የመጀመሪያዋ ግለሰብ የ33 አመት ሴት ስትሆን የጉዞ ታሪኳ ጅቡቲ፣ ብራዚል፣ ህንድ እና የመጨረሻ በረራዋ ኮንጎ ብራዛቪል ነው።
የቫይረሱን ምልክት በማሳየቷ በለይቶ ማቆያ ውስጥ ሆና በተደረገላት የላቦራቶሪ ምርመራ በኮሮና ቫይረስ መያዟ ማረጋገጥ ተችሏል።
ሁለተኛው ደግሞየ 26 ዓመት ወንድ ሲሆን የስራ ባህሪው ከተለያዩ ተጓዥ መንገደኞች ጋር ግንኙነት ያለው ሲሆን የቫይረሱን ምልክት በማሳየቱ በለይቶ ማቆያ ውስጥ ሆኖ በተደረገላት የላብራቶሪ ምርመራ በኮሮና ቫይረስ መያዙ ተረጋግጧል፡፡
እንዲሁም ሶስተኛው የ32 ዓመት ወንድ ሲሆን ቀደም ብሎ በቫይረሱ መያዙ ከተረጋገጠ ሰው ጋር ግንኙነት የነበረውና በለይቶ ማቆያ ውስጥ ሆኖ ክትትል ሲደረግለት የነበረ ሲሆን በተደረገለት የላቦራቶሪ ምርመራ በቫይረሱ መያዙን ማረጋገጥ ተችሏል፡፡
ሶስቱም በለይቶ ህክምና መስጫ ማዕከል የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው መሆኑን የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ገልጸዋል።
ከዚህ ባለፈም ከሰዎቹ ጋር ግንኙነት የነበራቸው ሌሎች ሰዎችን የመለይት ስራ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል፡፡
በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ በለይቶ ህክምና መስጫ ማዕከል የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው የሚገኙ 25 ሰዎች ሲሆኑ ሁለት ታማሚዎች በጽኑ ህሙማን ህክምና ክፍል ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑ ተጠቁሟል።
ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision