አዲስ አበባ ፣ ታኅሣሥ 12 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ትዊተርን በ44 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር የገዛው ቢሊየነር ኤሎን መስክ ከማህበራዊ ሚዲያው ዋና ስራ አስፈፃሚነት እንደሚለቁ አስታወቁ።
ኤሎን መስክ የኃላፊነት ቦታቸውን የሚያስረክቡት በትዊተር ገጻቸው ላይ “ራሴን ከሥራ አሥፈጻሚነት ቦታ ላግልል ወይ?” የሚል መጠይቅ ውሳኔ ይሰጥበት ዘንድ ለማኅበራዊ ትሥሥር ገጽ ተጠቃሚዎች ካጋሩ በኋላ በተሰበሰበው ውጤት መሰረት መሆኑን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የተሰበሰበው ውጤት እንደሚያሳየው 57 ነጥብ 5 በመቶዎቹ ቢሊየነሩ ከኃላፊነቱ እንዲለቁ ድምፅ ሰጥተዋል።
ለማኅበራዊ ትሥሥር ገጻቸው ተጠቃሚዎች ውሳኔ ተገዢ እንደሚሆን ቀደም ብለው ቃል የገቡት ኤሎን መስክ፥ የሥራ አስፈጻሚነት ቦታን የሚተካው ሰው ሲያገኝ አስረክባለሁ ብለዋል።
ኤሎን መስክ የሶፍትዌር እና የሰርቨር ቡድኑን ግን መምራት እንደሚቀጥሉ ነው ያመለከቱት።
ኤሎን መስክ ትዊተርን ገዝተው ከጠቀለሉ ጀምሮ ግማሽ የኩባንያውን ሰራተኞች ያሰናበቱ ሲሆን፥ በኩባንያው ውስጥ ያሳለፏቸው ውሳኔዎችም ወቀሳዎችን አስከትሎባዋል።