አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 7፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ከአቅርቦት አኳያ በከተማዋ የስኳር ምርት አቅርቦት ችግር ማጋጠሙን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ አስታወቀ፡፡
የቢሮው ምክትል ኃላፊ መስፍን አሰፋ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት፥ ለከተማው የተመደበው ኮታ 120 ሺህ ኩንታል ቢሆንም ላለፉት አራት ወራት እየቀረበ ያለው የስኳር ምርት መጠን ከግማሽ በታች ነው፡፡
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት እና ኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ ቁምነገር እውነቱ የቀረበው ቅሬታ ትክክል መሆኑን ገልጸው÷ በመንግሥት ድጎማ የሚቀርብ ስኳር የአቅርቦት እጥረት መኖሩን ተናግረዋል፡፡
እጥረቱን ለመቅረፍም ከስኳር አስመጪዎች ጋር በቅርብ ቀናት ውስጥ ውይይት ለማድረግ መታሰቡን እና ከስኳር አምራች ፋብሪካዎች ጋር ፍሬያማ ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡
እንዲሁም ከታኅሣሥ 15 እስከ 30 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ በስኳር ኮርፖሬሽን በኩል 2 ሚሊየን ኩንታል (200 ሺህ ቶን) ስኳር ወደ ሀገር ውስጥ ይገባል ብለዋል፡፡
የስኳር ምርት አቅርቦት እጥረቱ ከታኅሣሥ 30 ቀን 2015 ዓ.ም በኋላ እንደሚስተካከልም ነው የተናገሩት።
በዮሐንስ ደርበው