አዲስ አበባ፣ መጋቢት 22፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ከ15 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመቱ የተለያዩ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ።
የገቢዎች ሚኒስቴር የኮንትሮባንድ እቃዎቹ በለፉት 5 ቀናት በሀገሪቱ በሚገኙ በተለያዩ የጉምሩክ ኬላ ጣብያዎች የተያዙ መሆናቸውን አስታውቋል።
እነዚህ ህገ ወጥ ዕቃዎች ከ15 ሚሊየን 753 ሺህ ብር በላይ የሚገመቱ መሆናቸውም ነው የተገለጸው።
የኮንትሮባንድ ዕቃዎቹም የተለያዩ የአዋቂዎችና ህፃናት አልባሳት፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ ጊዜው ያለፈባቸው ምግቦች እና መጠጦች፣ ዘይትን ጨምሮ የክላሽ ጥይቶች እና ከብቶች ናቸው ተብሏል።
ህገ ወጥ እቃዎቹ በድሬዳዋ፣ በጅግጅጋ፣ ሞያሌ፣ ገናሌ፣ አዳማ፣ አዋሽ፣ ሀዋሳ እና በሌሎች የጉምሩክ ኬላ ጣብያዎች የተያዙ መሆኑም ተመላክቷል።
ኮንትሮባንድ እና ህገ ወጥ ንግድ በሀገርና በህዝብ ደህንነት ላይ ከፍተኛ ችግር እንደሚያስከትል በመረዳት ሁሉም ከመንግስት ጎን በመቆም ለችግሩ የመፍትሄ አካል እንዲሆን ጥሪ መተላለፉን ከገቢዎች ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡