አዲስ አበባ፣ መጋቢት 22፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) አካላዊ ርቀት በግብይት ስፍራዎች እና በትራንስፖርት መገልገያዎች ተግባራዊ እየተደረገ አለመሆኑ የኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ19) ለመከላከል የተቋቋመው ብሔራዊ ኮሚቴ ገለፀ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ19) ለመከላከል ከተቋቋመው ብሔራዊ ኮሚቴ የንዑሳን ኮሚቴ ኃላፊዎች ጋር በኢንተርኔት ውይይት ማካሄዳቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታውቋል።
በውይይቱ እንደቀረበው እያንዳንዱ ኮሚቴ ኮቪድ-19ን የመከላከል እና ሥርጭቱን የመግታት ተግባራትን በየድርሻው እያከወነ መሆኑ ተገልጿል።
ነገር ግን፣ የኮሚቴው አባላት ከተማይቱን በመመልከት ለመረዳት እንደቻሉት፣ አካላዊ ርቀት በግብይት ስፍራዎች እና በትራንስፖርት መገልገያዎች ተግባራዊ አልተደረገም ብለዋል።
ሃይማኖታዊ መሰባሰቦች ሥርጭቱን በመግታት ሥራው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደሩ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራዎች ከሕግ ማስከበር ተግባራት ጋር ተጣምረው የሚቀጥሉ ሲሆን፥ ሕዝቡ ቫይረሱን ለመከላከል የሚያስችሉትን ቅድመ ጥንቃቄዎች በሙሉ ተፈጻሚ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።