አዲስ አበባ፣መጋቢት 22፣2012(ኤፍ.ቢ.ሲ) በለንደን የሚገኙ የመርቼዲስ ሞተር አምራች ኢንጂነሮች
ከ100 ሰዓት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ለኮሮና ቫይረስ ህመምተኞች የሚረዳ የመተንፈሻ መሳሪያ አሻሽለው መስራታቸው ተሰማ፡፡
መሃንዲሶቹ ለንደን ውስጥ ከሚገኙ ክሊኒኮች እና የዩኒቨርሲቲ መሐንዲሶች ጋር በመተባበር በፊት በለንደን ከነበረው የአየር ግፊት መሳሪያ(ሲፒኤፒ )መሣሪያ ተሻሽሎ የተሰራ ነው ተብሏል፡፡
የሲፒኤፒ ማሽኖቹ የታካሚዎችን አየር መተላለፊያዎች እንዲከፈት ፣ አየር እና ኦክስጅንን በተከታታይ መጠን ወደ አፉ እና ወደ አፍንጫ በመገፋት ሳንባዎች ውስጥ የሚገባ የኦክስጂን መጠን እንዲጨምሩ የሚያደርግ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
ከዚህ ባለፈም በአንድ ግዜ ብዙ ማምረት የሚያስችል እና የቬንት ሌተር ፍላጎትን የሚቀንስ መሆኑ ነው የተነገረው።
አንድ መቶ የሚሆኑት አዳዲስ ዲዛይን የተደረገባቸው ማሽኖች ክሊኒካዊ ሙከራዎች ላይ ጥቅም ላይ ከመዋላቸውም ባለፈ በሀገሪቱ ዙሪያ ወደሚገኙ ሆስፒታሎች በፍጥነት እንደሚሰራጩ ተገልጿል፡፡
ክሊኒካዊ ሙከራዎችን ተከትሎ በቀን እስከ 1ሺህ የሚደርሱ መሳሪያዎችን ማምረት ይቻላልም ነው የተባለው፡፡
ከአንድ መቶ ሰዓታት ባነሰ ጊዜ ውስጥ የተሰራው ይህ ማሽን ምርቱን በጥቅም ላይ እንዲውል የብሪታንያ መድሃኒቶች እና የጤና እንክብካቤ ምርቶች ደንብ ኤጄንሲ መፍቀዱን የለንደን ዩኒቨርስቲ አስታውቋል፡፡
በሌላ በኩል አንዳንድ ባለሙያዎች የሲ.ፒ.ኤ.ፒ. ማሽኑ ጥቅም ላይ ሲውሉ ቫይረሱን የያዙ ጠብታዎች በመፍጠር የሆስፒታሉ ሠራተኞችላይ አደጋ ሊጥሉ ይችላሉ የሚል ስጋት እንዳሳሰባቸው ገልጸዋል፡፡
ነገር ግን የብሪታንያ ብሔራዊ የጤና አገልግሎት ሠራተኞች የግል መከላከያ መሳሪያዎችን እስከተጠቀሙ ድረስ ለበሽታው ያላቸው ተጋላጭነት ዝቅተኛ መሆኑን በመግለጽ ÷መሣሪያው የኮሮና ቫይረስ ህመምተኞችን ለማከም ስራ ላይ ይውላል ማለታቸው ነው የተገለጸው፡፡
በለንደን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ውስጥ የህክምና አማካሪ የሆኑት ፕሮፌሰር መርቫን ሲንገር በበኩላቸው ÷ እነዚህ መሳሪያዎች እጅግ በጣም ለታመሙ ሰዎች ጥቅም ላይ እንዲውሉ በማድረግ የሰዎችን ሕይወት ለማዳን ይረዳሉም ነው ያሉት፡፡
ምንጭ፡-ሲ.ኤን.ኤን