የሀገር ውስጥ ዜና

በተያዘው የመኸር ወቅት እስካሁን ከ42 በመቶ በላይ ምርት ተሰበሰበ

By Amele Demsew

December 05, 2022

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 26፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በዘንድሮው የምርት ዘመን በመኸር ወቅት በሰብል ከተሸፈነው 13 ነጥብ 4 ሚሊየን ሔክታር ከ42 በመቶ በላይ ያህሉ መሰብሰቡን የግብርና ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡ በምርት ዘመኑ በመኸር ወቅት 400 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለማግኘት መታቀዱን እና ለዚህም 13 ነጥብ 4 ሚሊየን ሔክታር በዘር መሸፈኑ ተገልጿል፡፡ እስካሁን ባለው ሂደት በዘር ከተሸፈነው አጠቃላይ ሔክታር በ5 ነጥብ 8 ሚሊየን ሔክታር ላይ የነበረው ምርት መሰብሰቡን በግብርና ሚኒስቴር የሰብል ልማት መሪ ሥራ አስፈጻሚ ኢሳያስ ለማ ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡ በተወሰኑ ሰብሎች ብቻ በኩታ ገጠም ይዘራ የነበረውን አሠራር በዚህ ዓመት ወደ አሥር የሰብል ዓይነቶች ማሳደግ መቻሉን ገልጸዋል፡፡ ዘመናዊ የምርት መሰብሰቢያ ማሽኖች በተሻለ መልኩ ሥራ ላይ እንዲውሉ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው በዚህም የምርት ብክነት በየዓመቱ እየቀነሰ ነው ብለዋል፡፡ አርሶ አደሩ መጋዘኖችን በማጽዳት ምርት እንዳይበላሽ በማድረግ ምርቱን ከብክነት የመታደጉን ሥራ እንዲያጠናክር ተጠይቋል፡፡