አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 20 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ተጨማሪ ሁለት ሰዎች ተገኙ።
በዚህም በኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ የተያዙት ሰዎች ቁጥር 21 መድረሱን የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ አስታውቀዋል።
በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጡት ግለሰቦች የ38 ዓመት ወንድ እና የ35 ዓመት ሴት የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያዊያን ናቸው።
ሁለቱም ግለሰቦች በተለያዩ ቀናት ወደ ዱባይ የጉዞ ታሪክ የነበራቸው ሲሆን የበሽታውን ምልክት በማሳየታቸው በተደረገላቸው የላብራቶሪ ምርመራ በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል።
በአሁኑ ሰዓት በለይቶ ህክምና መስጫ ማዕከል የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው ያሉ አስራ ሰባት (17) ታማሚዎች ሲኖሩ አንድ ታማሚ በጽኑ ህሙማን ህክምና ክፍል ክትትል እየተደረገላት ይገኛል፡፡
ከዚህ በፊት እንደተገለጸው ሁለቱ ታማሚዎች ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል፡፡
በተጨማሪም ከዚህ በፊት ከተጠቀሰው በተጨማሪ አንድ ታማሚ ሙሉ በሙሉ ያገገመ ሲሆን በአጠቃላይ ሁለት ታማሚዎች ሙሉ በሙሉ አገግመዋል፡፡
ነገር ግን ለጥንቃቄ ሲባል በለይቶ ማቆያ ክትትል እየተደረገላቸው ይገኛል፡፡