ዓለምአቀፋዊ ዜና

የኒውክሌር ባለቤት በሆኑ ሀገራት መካከል የሚፈጠር ግጭት ወደ ዓለምአቀፋዊ ጥፋት ያመራል – ሰርጌ ላቭሮቭ

By Alemayehu Geremew

December 02, 2022

አዲስ አበበ፣ ሕዳር 23፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኒውክሌር ባለቤት በሆኑ ሀገራት መካከል የሚፈጠር ማንኛውም ግጭት ወደ ዓለም አቀፋዊ የኒውክሌር ጦርነት ሊያመራ ይችላል ሲሉ የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ አስጠነቀቁ፡፡

ላቭሮቭ የኒውክሌር ባለቤት በሆኑ ሀገራት መካከል የሚኖር ማናቸውም ዓይነት መጎራበጥ በሠላማዊ መንገድ እና በመነጋገር ብቻ እንዲፈታ ያላሰለሰ ጥረት መደረግ አለበት ብለዋል።

የኒውክሌር ባለቤት ከሆኑ ሀገራት መካከል አንዱ ከሌላ ሀገር ጋር የተለመደው ዓይነት ግጭት ወይም ጦርነት ውስጥ ቢገባ ወደ ኒውክሌር ጦርነት የመሸጋገር ሰፊ ዕድል እንዳለውም ላቭሮቭ ሐሙስ ዕለት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ጠቁመዋል፡፡

ላቭሮቭ አሜሪካ እና ሩሲያ የኒውክሌር ዐቅማቸውን ለመቀነስ ሥልታዊ ዕቅድ ነድፈው እየተንቀሳቀሱ ነው በሚባለው ጉዳይ ላይ ምልከታቸውን እንዲያጋሩም ተጠይቀው እንደ ነበር አር ቲ ዘግቧል፡

በምላሻቸውም በፈረንጆቹ መስከረም 2021 ላይ ሩሲያ ወታደራዊ ዘመቻ በዩክሬን ላይ ከመጀመሯ ከረጅም ጊዜ በፊት ዋሺንግተን እና ሞስኮ ስትራቴጂያዊ የጦር መሳሪያዎችን ለመገደብ ውይይት ሲያደርጉ እንደነበር አስታውሰዋል።

ይሁን እንጅ ሀገራቱ ስምምነት ላይ ሳይደርሱ አሜሪካ ውይይቱን ማቋረጧንም ጠቁመዋል፡፡

የኒውክሌር ጦርነት አሸናፊ ስለሌለው እንዲጀመር መፍቀድ እንደማይገባም አስገንዝበዋል።