Johannes Hahn

ዓለምአቀፋዊ ዜና

ለሃንጋሪ የተፈቀደው 13 ቢሊየን ዩሮ እንዳይለቀቅ የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን ምክረ-ሃሳብ አቀረበ

By Alemayehu Geremew

November 30, 2022

አዲስ አበባ ፣ ሕዳር 21 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአውሮፓ ኅብረት ለሃንጋሪ የፈቀደው የ13 ቢሊየን ዩሮ የገንዘብ ድጋፍ እንዳይለቀቅ የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን ምክረ-ሃሳብ አቀረበ፡፡

የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን ÷ የገንዘብ ድጋፉ እንዲያዝ ሲል በምክንያትነት ያቀረበው ሃንጋሪ የአውሮፓን የኅግ የበላይነት ለማክበር ቁርጠኝነቷን አላሳየችም የሚል መሆኑን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል፡፡

ሃንጋሪ ከሁለት ቀናት በፊት ኅዳር 19 ቀን እስከ ተጠናቀቀው ቀነ ገደብ ድረስ በፍትኅ ሥርዓቷ ውስጥ ያሉትን 17 የማስተካከያ እርምጃዎች ልታሻሽል ለኅብረቱ ቃል ብትገባም እንዳለችው አልፈጸመችም፡፡

በዚህ ምክንያት ኅብረቱ ለሃንጋሪ ከመደበው በጀት 65 በመቶ ወይም 7 ነጥብ 5 ቢሊየን ዩሮ እንዳይለቀቅ ኮሚሽኑ አግዷል፡፡

በተጨማሪም ከአውሮፓ ኅብረት ለኮሮና ቫይረስ ማገገሚያ በሚል ሃንጋሪ የተፈቀደላትን የ 5 ነጥብ 8 ቢሊየን ዩሮ የገንዘብ ድጋፍ መያዙንም ባሮንስ የተሰኘው የዜና ምንጭ ዘግቧል፡፡

የአውሮፓ ኅብረት አባል ሀገራት በጉዳዩ ላይ ድጋፋቸውን ለመሥጠት አሊያም ለመቃወም ወይም የኮሚሽኑን ሐሳብ ለማስቀየር እስከ ታኅሳስ 19 ድረስ ድምጽ ይሠጣሉ፡፡