አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 19 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጃክ ማ ኢኒሼቲቭ በአፍሪካ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የተዘጋጁ የህክምና ቁሳቁሶችን ወደ ተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት እያደረሰ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ቻይናዊው ባለሃብት ጃክ ማ በጋራ በወሰዱት ኢኒሼቲቭ አማካኝነት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን በአፍሪካ ለመከላከል የሚያግዙ የሕክምና መርጃ ቁሳቁሶች ድጋፍ አዲስ አበባ መግባቱ ይታወሳል።
አየር መንገዱም የህክምና መርጃ ቁሳቁሶችን ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ወደ ተለያዩ ሃገራት በእቃ ጫኝ አውሮፕላኖቹ እያደረሰ ይገኛል።
እስካሁንም ከተደረገው ድጋፍ ግማሽ ያህሉን ወደ ሃገራቱ ማድረሱም ነው የተገለጸው።
ቀሪው የህክምና ቁሳቁስ ስርጭትም በቀጣይ ቀናት ከየሃገራቱ የአውሮፕላን ማረፊያ ፍቃድ ሲገኙ የሚቀጥል ይሆናልም ነው የተባለው።
ስርጭቱ በኢትዮጵያ አየር መንገድ አመራርና የሥርጭት ሥራውን ለመከታተል በተቋቋመው ኮሚቴ አማካኝነት እየተከናወነ እንደሚገኝም ተገልጿል።
ቻይናዊው ባለሃብት ጃክ ማ ለ54 የአፍሪካ ሀገራት የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ለሚደረገው ጥረት የሚውል የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጋቸው ይታወሳል።
በዚህም እያንዳንዱ የአፍሪካ ሃገር ቫይረሱን ለመለየት የሚረዱ 20 ሺህ መመርመሪያዎች፣ 100 ሺህ የፊት ጭምብል፣ የህክምና ባለሙያዎች የሚለብሷቸው 1 ሺህ መከላከያ ልብሶችን ጨምሮ የተለያዩ ድጋፎች ይደረግለታል።
ድጋፉም በኢትዮጵያ አማካኝነት ለሁሉም የአፍሪካ ሃገራት እየተዳረሰ ይገኛል።