Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የሰራተኛውንና የስራ አመራሩን ከኮሮና ቫይረስ መከላከል የሚያስችል የስራ ቦታ ምላሽ ፕሮቶኮል ወጣ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 18፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የሰራተኛውንና የስራ አመራሩን ከኮሮና ቫይረስ ለመከላከል የሚያስችል የስራ ቦታ ምላሽ ፕሮቶኮል ወጣ።

የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ በፍጥነት እየተስፋፋ በመጣው የኮሮና ቫይረስ ምክንያት የአሰሪና ሰራተኛ ግንኙነቱን እንደወትሮው ማስቀጠል ፈታኝ መሆኑን አንስተዋል።

በዚህም ዛሬ የወጣው ፕሮቶኮል በሶስትዮሽ ወይም በመንግሥት፣ በአሰሪና በሰራተኛው መካከል ተግባራዊ የሚያደረግ ነው ብለዋል።

አሁን ላይ ቫይረሱ በሃገሪቱ ዋና ዋና የስራ ዘርፎችና ኢኮኖሚው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩ በመረጋገጡ ፕሮቶኮሉ በወረርሽኙ ታሳቢ ሁኔታዎች ላይ ተመስርቶ ተፈጻሚ እንደሚሆንም ተናግረዋል።

ፕሮቶኮሉ የኮሮና ወረርሽኝ በሃገሪቱ ኢኮኖሚ፣ በድርጅቶች ቀጣይነትና ህልውና፣ በሰራተኞች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ላይ የሚፈጥረውን ጉዳት ለመቀነስ የሚያግዝ መሆኑንም ገልፀዋል።

የስራ ቦታ ምላሽ ፕሮቶኮሉ በመሰረታዊ የስራ ቦታ የቫይረሱ መከላከያ ስልቶችና አሰሪና ሰራተኛን በተመለከተ ደረጃ በደረጃ ሊወሰዱ በሚገባቸው ህጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃዎች ስር አሰሪና ሰራተኞች እንዲሁም የደህንነት ኮሚቴዎች ሊወስዷቸው የሚገቡ ጥንቃቄዎችን እና ዝርዝር ነጥቦችን የያዘ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ፕሮቶኮሉ የኢትዮጵያ ሰራተኛ ማህበራት፣ የኢንዱስትሪ አሰሪዎችና የአሰሪዎች ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንቶች በተገኙበት ነው የፀደቀው።

የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርም ከዛሬ ጀምሮ የፕሮቶኮሉን አተገባበር ይከታተላል ተብሏል።

 

በሶዶ ለማ

Exit mobile version