አዲስ አበባ፣ ሕዳር 12፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት አራት ወራት ከ162 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የገቢዎች ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የገቢዎች ሚኒስትር ወይዘሮ አይናለም ንጉሴ ÷ሚኒስቴሩ ባለፉት አራት ወራት 166 ነጥብ 52 ቢሊየን ብር ገቢ ለመሰብሰብ አቅዶ 162 ነጥብ 99 ቢሊየን ብር መሰብሰቡን ገልፀዋል፡፡
ከተሰበሰበው ገቢ ውስጥ 105 ነጥብ 24 ቢሊየን ብር የሚሆነው ከሀገር ውስጥ ታክስ ገቢ የተሰበሰበ ሲሆን ቀሪው 57 ነጥብ 74 ቢሊየን ብር ደግሞ ከወጪ ንግድ ቀረጥ እና ታክስ የተሰበሰበ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ባለፉት አራት ወራት በህገ-ወጦች አማካኝነት መንግስት ሊያጣው የነበረን 11 ነጥብ 169 ቢሊየን ብር ገቢ ማዳን መቻሉም ተገልጿል፡፡
እንዲሁም ተቋሙ ባለፉት አራት ወራት ከአዲስ እና ከቆየ የታክስ ዕዳ 11 ነጥብ 10 ቢሊየን ብር ገቢ ለመሰብሰብ አቅዶ 12 ነጥብ 72 ቢሊየን ብር መሰብሰብ መቻሉን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡