ስፓርት

ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ተካሔደ

By Shambel Mihret

November 20, 2022

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 11፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ታዋቂ አትሌቶችን ጨምሮ ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች የተሳተፉበት ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በአዲስ አበባ ከተማ ተካሂዷል፡፡

በሩጫው የማስጀመሪያ ሥነ ስርዓት ላይ÷ ፕሬዚዳንት ሳኅለወርቅ ዘውዴ፣ የባሕልና ስፖርት ሚኒስትር ቀጄላ መርዳሳ፣ የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናኒሴ ጫሊ እና የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች፣ ተጋባዥ እንግዶች፣ ታዋቂ አትሌቶች እና የሩጫው ተሳታፊዎች ተገኝተዋል።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ÷ አብረን ስንሆን እናምራለን፤ ኢትዮጵያም ከፍ ትላለች ብለዋል፡፡

ታላቁ ሩጫ ለከተማችን ከስፖርታዊ ውድድርነቱ ባሻገር የአብሮነት፣ የሰላምና የፍቅር እንዲሁም የትብብር ተምሳሌት ጭምር ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በ1994 ዓ.ም በአትሌት ኃይሌ ገብረ ሥላሴ የተጀመረ ሲሆን÷ በአፍሪካ ቀዳሚ በዓለም ደግሞ ሥድስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ትልቅ የጎዳና ላይ ሩጫ ነው፡፡

ዛሬ የተካሔደው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ መነሻው እና መጨረሻው መስቀል ዐደባባይ ሲሆን÷ አጠቃላይ እርቀቱም 10 ኪሎ ሜትር ነው፡፡

ከዚህኛው ሩጫ ቀደም ብሎ የአካል ጉዳተኞች ውድድር ተካሂዷል፡፡