የሀገር ውስጥ ዜና

የአሰራርና የአገልግሎት አሰጣጥ ስርዓትን ማዘመን የሚያስችል የሶስትዮሽ ስምምነት ተፈረመ

By Tamrat Bishaw

November 18, 2022

አዲስ አበባ ፣ ሕዳር 9 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአሰራርና የአገልግሎት አሰጣጥ ስርዓትን ማዘመን የሚያስችል የሶስትዮሽ ስምምነት ተፈረመ።

ስምምነቱን የተፈራረሙት የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን፣ የኢትዮጵያ ሆርቲካልቸር አምራችና ላኪዎች ማህበር እና ኢስት አፍሪካ ትሬድ ማርክ የተሰኘ ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት ናቸው።

በመግባቢያ ስምምነቱ መሰረትም የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን እና የኢትዮጵያ ሆርቲካልቸር አምራችና ላኪዎች ማህበር አገልግሎት አሰጣጣቸውን በዘመናዊ የዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘ ለማድረግ የሚያስችል እንደሆነ ተገልጿል።

የተቋማቱን የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ መሰረተ ልማት ግንባታ በማሳደግ የአሰራርና የአገልግሎት አሰጣጥ ስርዓታቸውን ማዘመን የስምምነቱ አላማ መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ድሪባ ኩማ፥ ሰምምነቱ ተቋሙ በዲጂታል ቴክኖሎጂ በታገዘ መልኩ ዘመናዊ አገልግሎት እንዲሰጥ የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከዚህ አኳያ ሶስቱም ተቋማት ስምምነቱን ሀገር አቀፍ ለውጥ በሚያመጣ መልኩ ተግባራዊ ለማድረግ እንደሚሰሩም ነው የተናገሩት።

የኢትዮጵያ ሆርቲካልቸር አምራችና ላኪዎች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ዘላለም መሰለ፥ ስምምነቱ በዘርፉ ያለውን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት እንደሚያሳድገው ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡

የኢስት አፍሪካ ትሬድ ማርክ በኢትዮጵያ ዳይሬክተር አቶ እውነቱ ታየ በበኩላቸው፥ ስምምነቱ በዘርፉ ያለውን የግብይት ስርዓት ለማዘመን እንደሚያግዝ ጠቁመው ለተግባራዊነቱም ቀጣይነት ያለው ስራ እንደሚከናወን አረጋግጠዋል።