Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የሰላም ስምምነቱ ኢትዮጵያን ያኮራ አፍሪካዊ ድል ነው – አቶ ደመቀ መኮንን

አዲስ አበባ ፣ ሕዳር 9 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በፕሪቶሪያ የተደረሰው የሰላም ስምምነት ውጤት ኢትዮጵያን የሚያኮራ አፍሪካዊ ድል መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ተናገሩ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሰራተኞች ገለፃ ያደረጉ ሲሆን ከሰራተኞቹ ለተነሱ ጥያቄና አስተያየትም ማብራሪያ እና ምላሽ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸውም መንግስት ሀገሪቱ ወደ ሰላም እንድትመለስ ፅኑ ፍላጎት እያሳየ መምጣቱን ጠቅሰው፥ በፕሪቶሪያ የተደረሰው ስምምነት የመንግስትን ቁርጠኛ የሰላም ፍላጎት ያረጋገጠ እና ለህዝብ ያለውን እውነተኛ ወገንተኛነት የሚገልፅ መሆኑን አመላክተዋል።

ስምምነቱ ኢትዮጵያ ሁልጊዜም በምታንፀባርቀው ለአፍሪካዊ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ መርህ መደረጉ ኢትዮጵያን የሚያኮራ ለህዝብ ዘላቂ ሰላም ሊያመጣ የሚችል አፍሪካዊ ድል መሆኑንም አንስተዋል።

የተገኘው ውጤትም ለውጭ ግንኙነት እና ዲፕሎማሲ ስራ አጋዥ መሆኑን በማንሳት፥ ሰራተኛው ይህን በመገንዘብ ሀላፊነቱን በብቃት እንዲወጣም አስገንዝበዋል።

በመድረኩ በስምምነቱ ላይ በተደረሱ ጭብጦች፣ የድርድር ሁኔታና እና ቀጣይ ሂደቶች ላይ ገለፃ የተደረገ ሲሆን ይህንን መነሻ በማድረግም ውይይት ተካሂዷል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version