ሕዳር 4፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በትዕግስት እና በጥንቃቄ የምታደርገው ውሳኔ ለሁሉም ልጆቿ ጥቅም ስትል መሆኑን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ ተናገሩ።
ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባስተላለፉት መልዕክት፥ “ከታሪክና ተግባራዊ ልምምድ አንጻር ነገሮችን ከተመለከትን ከግጭት ወደ ዘላቂ ሰላም የሚደረግ ሽግግር በሰጥቶ መቀበል መርህ፣ በትዕግስትና በብልሃት የሚመሩ መሆኑን ያመለክተናል” ብለዋል።
ለዘላቂ ሰላም ጥቅሞችን ማጣጣም የግድ እንደሆነም ነው ያመለከቱት።
ይህ ጉዳይ ውስጣዊ ከሆነ ደግሞ የተለየ ትኩረት እና ማስተዋልን እንደሚጠይቅ ዶክተር ለገሰ ገልፀዋል።
“ኢትዮጵያ በትዕግስት እና በጥንቃቄ የምታደርገው ውሳኔ ለሁሉም ልጆቿ ጥቅም ስትል ነው” ብለዋል።
“ጉዳቶቻችንና ሃዘናችንን የምንረሳው ይቅር ስንባባል ነው” ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል።
ለዚህ መሳካት ልጆቿም ይተባበራሉ ብላ ኢትዮጵያ በእኛ ላይ እምነት ጥላለች ያሉት ሚኒስትሩ፥ “ከዚህ አኳያ የጀመርነው መንገድ መልካም ይመስላል፤ ልጆቿ ከተባበሩ ይሳካል” ብለዋል።