አዲስ አበባ፣ ሕዳር 1፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ)16ኛው የአፍሪካ ወጣቶች ቀን “የወጣቶች ንቁ ተሳትፎና ተካታችነት ለሰብዕና ልማት” በሚል መሪ ሐሳብ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ዛሬ መከበር ጀምሯል።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የወጣቶች ተሳትፎና አደረጃጀት አቅም ግንባታ ዴስክ ሃላፊ ኩራ ጀማነህ እንዳሉት÷ ቀኑን በማስመልከት “ትምህርትና የወጣቶች ሰብዕና” በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ሰነድ ቀርቦ ውይይት ይደረጋል።
ወጣቶች ተሳትፏቸውን ለማሳደግ የበኩላቸውን ሚና በግንባር ቀደምትነት ሊወጡ እንደሚገባ ጠቅሰው ለዚህም የባለድርሻ አካላት ድጋፍ ወሳኝ መሆኑን አስታውቀዋል።
በመርሀ-ግብሩ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ እና የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋን ጨምሮ የፌዴራል እና የደቡብ ክልል የስራ ሃላፊዎች፣ የአፍሪካ ህብረት ተወካዮች፣ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች፣ የጋሞ ሀገር ሽማግሌዎች ተገኝተዋል።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ በመድረኩ እንዳሉት ÷ ወጣትነት በርካታ አካላዊ፣ ስሜታዊ፣ እዕምሯዊና ስነልቦናዊ ለውጦች የሚስተዋልበት፣ ለቀጣይ ህይወትና ማንነት መሰረት የሚጣልበት፣ ባህላዊ እሴቶችና ልምዶች የሚቀሰሙበት፣ ዝንባሌና ተሰጥዖን ለመለየት ጥረት የሚደረግበት ወርቃማ የእድሜ ዘመን መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
በመሆኑም በትምህርት ቤት አካባቢ ወጣቶችን ለሱስና ለአልባሌ ስብዕና የሚዳርጉና የሚገፋፉ ተግባራት እንዳይከናወኑ ተገቢውን ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
በተለይ የወጣቶች ስብዕና እንዲገነባ በማስቻል ረገድ ከቤተሰብ፣ ከሃይማኖትና ከሚዲያ ተቋማት ሚናቸው እጅግ የላቀ ነው ማለታቸውን ከሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
የትምህር ሚኒስትሩ ፕሮፊሰር ብረሀኑ ነጋ በበኩላቸው÷ ትምህርት የሁሉነገር መሰረት በመሆኑ ወጣቶች በራስ መተማመን በመፍጠር እራሳቸውን ከቻሉ ትክክለኛ የአገር ተረካቢ ዜጎች እንዲሆኑና በአቋራጭ ወይም በስረቆሽ የሚገኝን ውጤት የሚጠየፍ ዜጋ መፍጠር ተገቢና ዋናው ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡
መርሃ ግብሩን ያዘጋጁት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ ጋር በመተባበር ነው፡፡